የበለፀገው ሶፍት ዌር የትራፊክ ፍሰቱን የሚያዘምን የዜጎችን እንግልት የሚቀንስ ነው ። ዶ/ር ጀማሉ ጀንበር
ከተማ አስተዳደሩ የትራንስፖርት ስርዓቱን ለማዘመን እና የቁጥጥር ስርዓቱን በቴክኖሎጂ ለማገዝ ሰፊ ስራዎች እየተሰራ ነው ያሉት ዶ/ር ጀማሉ ጀንበር በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ ከተማ ፐብሊክ ሰርቪስ እና የሰው ሀብት ቢሮ ኃላፊ ናቸው።
ዛሬ በይፋ ያስጀመርነው የበለፀገው ሶፍት ዌር የትራፊክ ቁጥጥርና የፖርኪንግ አስተዳደር ስርዓት የትራንስፖርት ፍሰቱን የሚያዘምን ፣ የህዝቡን እንግልት የሚቀንስ እና ኢኮኖሚያዊ ፣ ፖለቲካዊና ማህበራዊ ፋይዳው የጎላ ነው ሲሉ ተናግረዋል።
ዶ/ር ጀማሉ አክለውም አዲስ አበባ ስሟን የሚመጥን የመንገድ መሰረተ ልማት እየተከናወነ በሚገኝበት እና የስማርት ሲቲ ደረጃን እንድታሟላ በርካታ ሪፎርሞችን እያከናወነች ባለችበት ወቅት የትራፊክ ማኔጅመንት ሲስተም ሶፍት ዌር በልፅጎ ለትግበራ መብቃቱ የከተማችንን በቴክኖሎጂ አገልግሎት የመስጠት እና የመቆጣጠር ስራን አንድ እርምጃ ወደፊት የሚያራምድ ነው ብለዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የትራፊክ ማኔጅመንት ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ክበበው ሚዴቅሳ በበኩላቸው ሲስተሙ በዋናነት ቀደም ሲል በማኑዋል ሲሰራ የነበረ አንዳንድ የቁጥጥር ብልሹ አሰራርን የሚያስቀር ለትራፊክ ቅጣት ፓድ ህትመት ወጪን የሚያድን ፣የትራፊክ ደንብ ተላላፊዎች ታርጋ ሲፈታ እና መንጃ ፈቃድ ሲወስድባቸው መልሰው ለመውሰድ የነበረውን ውጣ ውረድ የሚገታና በአጠቃላይ ከደንብ መተላለፍ የእርምት እርምጃ አወሳሰድ ጋር የነበሩ ሰው ሰራሽ ችግሮችን ከመቅረፍም በላይ ሲስተሙ ከፖርኪንግ አገልግሎት ክፍያ ጋርም የሚያያዝ በመሆኑ ቀደም ሲል በፓርኪንግ አገልግሎት ዙሪያ የሚታዩ ችግሮችንም ይፈታል ሲሉ ተናግዋል።
የበለፀገው ሶፍት ዌር በመንገድ ትራፊክ መቆጣጠሪያ ደንብ 395/2009 ላይ የነበሩ ክፍተቶችን እንደ አዲስ መካተት ያለባቸውን በጥናትና ባለድርሻ ተቋማትን ባሳተፈ መልኩ በመለየት ደንብ 557/2016 በመፀደቅና ከሲስተም ጋር በመቀናጀት የተሰራ መሆንንም ዳይሬክተሩ አክለዋል።
አያይዘውም እንዳሉት በዚህ ወቅት ሲስተሙን ወደ ተግባር ለማስገባት የሚያስችሉ ግብዓቶች ተሟልተው ዝግጅት የተደረገ ሲሆን ከአሽከርካሪ እና ተሽከርካሪ ፈቃድና ቁጥጥር ባለስልጣን ከኢትዮጵያ ቴሌኮም ቴሌ ብር ጋር ፣ከባንኮች ጋር የማስተሳሰሩና የማቀናጀቱ ስራ ሙሉ በሙሉ ተጠናቋል ብለዋል።
የአዲስ አበባን ትራንስፖርት ለማሻሻልና አስተማማኝ ፣ ተደራሽ ፣ ደህንነቱ የተጠበቀ ምቹ ለማድረግ እየተሰራ ነው ያሉት የአዲስ አበባ ከተማ ትራንስፖርት ቢሮ ኃላፊ አቶ ያብባል አዲስ የትራፊክ ማኔጅመንቱን ማዘመንና የቁጥጥር ስርዓቱን በቴክኖሎጂ መደገፍ አንዱ ነው ብለዋል።
ለተጨማሪ የመረጃ አማራጮች
https://linktr.ee/addisababacommunication
Comments
ምንም አልተገኘም.
አስተያየቶችዎን ይተዉት.