
በወቅታዊ የጤና አገልግሎት ዙሪያ ከጤና ሚኒስቴር የተሰጠ መረጃ
የጤና ሚኒስቴር ለማኅበረሰባችን ጥራቱን የጠበቀ እና ፍትሐዊ የጤና አገልግሎትን ተደራሽ ለማድረግ የጤና ፖሊሲ እና ስትራቴጂ በመቅረጽ የኅብረተሰቡን ባለቤትነት ባረጋገጠ መልኩ ሥራዎችን በትኩረት እያከናወነ መሆኑ የዐደባባይ ሐቅ ነው።
ምክንያቱም መቼምና በምንም ሁኔታ መቋረጥ ከሌለባቸው ማኅበራዊ አገልግሎቶች አንዱ የጤና አገልግሎት በመሆኑ፤ ስለዚህም ዛሬን ጨምሮ ባለፉት ቀናት በመላ ሀገራችን በሚገኙ የጤና ተቋማት እንደ ወትሮው ሁሉ መደበኛ የጤና አገልግሎቶች ለማኅበረሰባችን ያለምንም መቆራረጥና መስተጓጎል እየተሰጡ ይገኛሉ።
ይሄንን የተረዳው የጤና ባለሞያ በማኅበራዊ ሚዲያ በሚሠራጩ የተሳሳቱ መረጃዎች ጫና ሳይገፋ የገባውን የሞያ ቃል ኪዳን እና መሐላ ጠብቆ ማኅበረሰቡን እያገለገለ በመሆኑ ምስጋና ይገባዋል።
ይሁን እንጂ በጥቂት የማስተማሪያ የጤና ኮሌጆች/ተቋማት በመደበኛ የሥራ ገበታቸው ላይ ያልተገኙ የተወሰኑ ባለሞያዎች እንዳሉ መረጃዎች ደርሰውናል። ከእነዚህ የጤና ባለሞያዎች መካከል ብዙዎቹ በሐሰተኛ መረጃ የተወናበዱ ሲሆኑ ጥቂቶቹ ደግሞ ጥፋትን ዓላማቸው ያደረጉ ናቸው።
ድርጊቱ የራስን ቤተሰብ፣ ዘመድ፣ ወገን እና መላውን ማኅበረሰብ ከመጉዳት ባለፈ ከሞያ ሥነ ምግባር፣ ከሰብአዊነት አኳያ ተቀባይነት የሌለው ተግባር ነው።
ከሕግ አኳያም የጤና ሞያ የሥራ ማቆም አድማ ከማይደረጉባቸው የሥራ ዘርፎች መካከል አንዱ መሆኑ በግልጽ ተደንግጓል። የጤና ባለሞያዎች ጥያቄ እንኳን ቢኖራቸው በሥራ ገበታቸው ተገኝተው መደበኛ ሥራቸውን እያከናወኑ ጉዳያቸውን ለሚመለከተው አካል ማቅረብ ይጠበቅባቸዋል።
በመሆኑም እነዚህ የጤና ባለሞያዎች ወደ ሥራ ገበታቸው ተመልሰው ማኅበረሰባቸውን እንዲያገለግሉ በየተቋማቸው ጥሪ ተደርጓል።
መንግሥት የጤና ባለሞያውን ዘላቂ ተጠቃሚነት ባረጋገጠ መልኩ በጥናት ላይ የተመሠረተ መፍትሔ ለመስጠት ቀደም ብሎ የጤና አገልግሎት አስተዳደርና ቁጥጥር አዋጅ 1362 /2017 አጸድቆ ደንብና መመሪያዎችን በማውጣት ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ ይገኛል።
በጎ ኅሊና ያላቸው የጤና ባለሞያዎች ይህንን በመገንዘብ ሥራቸውን በአግባቡ እንዲያከናውኑ የሚኒስቴር መሥሪያ ቤታችን በዚሁ አጋጣሚ ጥሪ ያቀርባል።
በሌላ በኩል ደግሞ ኅብረተሰቡ በተለያዩ ማኅበራዊ ሚዲያዎች በሚሠራጩ የሐሰት መረጃዎች ሳይረበሽ የሚፈልገውን የጤና አገልግሎት በተለመደው መልኩ በጤና ተቋማት ማግኘት እንደሚችል እናሳውቃለን።
መንግሥት በሆደ ሰፊነት ችግሩን ለመፍታት ያሳየውን ትዕግሥት ወደጎን በመተው በሥራ ገበታቸው ላይ ባልተገኙ እንዲሁም በጤና ተቋሙም ሆነ ከጤና ተቋሙ ውጭ ሆነው ሁከትና ብጥብጥ በሚፈጥሩት ላይ አስፈላጊ የሆነ ሕጋዊ እርምጃ የሚወሰድ መሆኑን ቀድመን እናሳውቃለን።
የጤና ሚኒስቴር
ግንቦት 07፣ 2017 ዓ.ም
Comments
ምንም አልተገኘም.
አስተያየቶችዎን ይተዉት.