"ቃልን በተግባር ለኢትዮጵያ ብልፅግና "
በብልፅግና ፓርቲ የሁለት ዓመት ተኩል አፈፃፀም እና ቀጣይ አቅጣጫዎች ላይ የመከረው ከተማ አቀፍ የአባላት ኮንፈረንስ የጋራ ተግባቦት በመፍጠር ተጠናቋል ።
የአዲስ አበባ ከንቲባ ክብርት አዳነች አቤቤ በኮንፈረንሱ ላይ እንደተናገሩት ኮንፈረንሱ ለህዝባችን ከገባነው ቃል እና ካስቀመጥነው ግብ አንፃር አፈፃፀማችን ላይ እኩል አረዳድ በመያዝ በጋራ ለመረባረብ መሆኑን አስገንዝበዋል።
ብልፅግና ለሀሳብ ልዕልና ክብር የሚሰጥ ፓርቲ መሆኑን የገለፁት ክብርት ከንቲባዋ የአባላት ሀሳብን በሀሳብ የማሸነፍ ባህል እንዲዳብርም በትኩረት መሰራቱን አስረድተዋል።
ያለችን አንዲት አገር በመሆኑና ለሁለንተናዊ ብልፅግና የሚተጋ ፓርቲ በመሆኑ የተፎካካሪ ፓርቲ አመራሮች በየደረጃው በሚገኙ የአስፈፃሚው አካል መዋቅሮች አሻራቸውን እንዲያሳርፉ የማድረግ አዲስ ታሪክ መሰራቱንም ጠቅሰዋል።
ብልፅግና ፓርቲ ለህዝባችን ህይወት መሻሻል እንደሚሰራ የጠቀሱት ክብርት ከንቲባዋ ፕሮጀክቶቻችን ሁሉ የሰውን ህይወት የሚያለመልሙ ሰው ተኮር መሆናቸውን አውስተዋል።
የብልፅግና ፓርቲ አመራርና አባላት መለኪያ ውጤታማነትና ሌብነትን መታገል በመሆኑ የሀሳብ ጥራትን በመያዝ ሌብነትን ፣ ልግመኝነትን፣ የአገልግሎት አሰጣጥ ብልሹ አሰራሮችን በፅናት መታገል እንደሚገባም አብራርተዋል።
ለአንድ ዓላማ በመረባረብ ቃልን በተግባር ማዋልና የህዝባችንን የኑሮ ጫና ለማቃለል የተጀማመሩ ሰው ተኮር ስራዎችን ማጠናከር እንደሚገባም አሳስበዋል።
በብልፅግና ፓርቲ የአዲስ አበባ ቅ/ፅ/ቤት ሀላፊ አቶ ሞገስ ባልቻ ወንድማማችንትን በማጠናከር ህብረ ብሔራዊ የፌዴራል ሰርዓትን በማረጋገጥ የአገር ግንባታን ለማጠናከር ፣ የምግብ ዋስትናን ከማረጋገጥ የተሻገረ ኢኮኖሚያዊ ድልን ለማስመዝገብ ፣ ተቋማዊ መሰረት ያለው ዴሞክራሲን ለመገንባት እንዲሁም ፍትሀዊ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ ባለፉት ሁለት ዓመት ተኩል የተቀናጀ ርብርብ መደረጉ አውስተዋል።
ሜጋ ፕሮጀክቶችን ጀምሮ የመጨረስ ባህል ላይ ከመጣው አበረታች ውጤት በተጨማሪ ትምህርትን በመሳሰሉ ማህበራዊ ልማቶችም ዓለም አቀም እውቅና ጭምር የተቸረው ስኬት መመዝገቡን ጠቅሰዋል።
ዋነኛ ትኩረታችን ጉድለቶቻችንን መሙላት ቢሆንም የተፈፀሙትን እና ያልተፈፀሙትን ቆጥሮ መለየት ለላቀ ድል አጋዥ መሆኑን የጠቆሙት ሀላፊው በኮንፈረንሱ የጋራ ርብረብ የሚደረግባቸው የሀሳብ ግብአቶች መገኘታቸውን ገልፀዋል።
ፓርቲያችን በወጣት ሀይል የተሞላ መሆኑን ያስረዱት አቶ ሞገስ በከተማ ደረጃ 70 በመቶ አመራሮች ወጣቶች መሆናቸውንና ተተኪና ኮር አመራሮችን ለማበራከትም በትኩረት እንደሚሰራ አመላክተዋል።
አባላት አቅማቸውን በመገንባት ለላቀ ተልዕኮ ብቁ የሚሆኑባቸውን ህዋሳትንና መሰረታዊ ድርጅቶችን ማጠናከር እንደሚገባም አሳስበዋል።
ምክትል ከንቲባ አቶ ጃንጥራር አባይ ባለፉት ዓመታት ሲንከባለሉ የመጡ የህዝባችንን ጥያቄዎች ለመመለስ ርብርብ መደረጉን ጠቁመው የኑሮ ውድነቱን ለማረጋጋትም የሸማች ማህበራትን በቴክኖሎጂ ለማዘመን ሪፎርም መጀመሩን በምርትና ምርታማነት ላይም በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰዋል።
ህዝባችን ኣገልግሎት በነፃ የማግኘት መብቱን ማረጋገጥ ይገባል ያሉት አቶ ጃንጥራር አባላት ግንባር ግንባር ቀደም ሚናቸውን እንዲወጡ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
ባለፉት ሁለት ዓመት ተኩል ፓርቲያችን ለህዝባችን የገባቸውን ቃሎች በመፈፀም ያስመዘገባቸው ተጨባጭ ስኬቶች ለቀጣይ ርብርብም ተነሳሽነታቸውን ከፍ እንዳደረጉላቸው የጠቆሙት የአባላት ኮንፈረስ ተሳታፊዎች እንደ ከተማ ትኩረት ይሻሉ ያሏቸውን የተለያዩ ሀሳቦችንም አቅርበዋል።
በፓርቲያችን መሪነት እየተከናወኑ ካሉ አንፀገራዊ ድሎችን ወደ ኋላ ሊመልሱ የሚችሉ ሌብነትንና ብልሹ አሰራሮችን ፣ የአገልግሎት አሰጣጥ ችግሮችን ፣ ፅንፈኝነትን እና የመሳሰሉ ተግዳሮቶችን በጋራ ታግሎ ማረም እንደሚገባ የኮንፈረንሱ ተሳታፊዎች ሀሳባቸውን አንፀባርቀዋል።
ከተማ አቀፍ የአባላት ኮንፈረንሱ ተቀራራቢ የሀሳብና የተግባር አንድነት በመያዝ ሪፎርሙን ለማስቀጠል ፣ ብልፅግና ፓርቲ ሳንካዎች ብሎ የለያቸውን ሌብነትንና ፅንፈኝነትን ለመታገል፣ የወጣቶችና የሴቶችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚደረጉ ጥረቶችን ለማጠናከር ፣ የመልካም አስተዳደርና የአገልግሎት አሰጣጥ ችግሮችን ታግሎ ለማስተካከል ፣ ሜጋ ፕሮጀክቶችንና የልማት ኮርደር የላቀ አፈፃፀም በማስቀጠል ቃልን በተግባር ለመተርጎም የጋራ ርብርብ እንደሚደረግ በአቋም መግለጫው አረጋግጧል።
Comments
ምንም አልተገኘም.
አስተያየቶችዎን ይተዉት.