
በህዝብ ድምፅ የመጣ መንግስት በመሆኑ በየጊዜው ህዝብን ማዳመጥ ፣ ብዥታዎችን ማጥራት ፣ ችግሮችን በጋራ የመፍታት ጥረቱ ተጠናክሮ ይቀጥላል- አቶ ሞገስ ባልቻ
"ትውልድ በመምህራን ይቀረፃል ፤ ሀገር በትምህርት ይበለፅጋል ! "
የኮተቤ ትምህርት ዩኒቨርስቲ መምህራን እና ሰራተኞች "ትውልድ በመምህራን ይቀረፃል ፤ ሀገር በትምህርት ይበለፅጋል ! " በሚል ርዕስ በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ተወያይተዋል።
በብልፅግና ፓርቲ የአዲስ አበባ ቅ/ፅ/ቤት ኃላፊ እና የኮተቤ ትምህርት ዩኒቨርስቲ ምክትል የቦርድ ሰብሳቢ አቶ ሞገስ ባልቻ ባቀረቡት የመወያያ ሰነድ ከሀገራዊ ለውጡ በኋላ የፖለቲካ ስብራቶችን ለመጠገን የፖለቲካ ምህዳሩን በማስፋት ፣ ትክክለኛ የፌዴራሊዝም ስርዓት እንዲጎለብት በማድረግ ፣ ለህልውና ስጋት የሚያጋልጡ ችግሮችን በመቅረፍ አበረታች ጥረቶች እየተደረጉ መሆናቸውን አስገንዝበዋል።
ሀሳብን በሀሳብ ከመታገል ይልቅ አፍራሽ የፅንፈኝነት አካሄድን የሚከተሉ ግለሰቦችና ቡድኖች መኖራቸው ፣ ከወል ትርክት ይልቅ ነጠላ ትርክት ጎልቶ መውጣቱ ፣ ፖለቲካዊ ፍላጎትን በሀይል ለማሳካት መጣር ፣ ነፃነትን በአግባቡ የማስተዳደር ችግር እና በተቋም ግንባታ ላይ ያሉ ክፍተቶች ደግሞ በቀጣይም የሁሉንም ርብርብ የሚጠይቁ ጉዳዮች መሆናቸው ተጠቅሷል።
ብዝሀ ዘርፍ ኢኮኖሚን ተግባራዊ በማድረግ እና የግሉን ዘርፍ ሚና በማላቅ በግብርና ፣ በኢንዱስትሪ ፣ በቱሪዝም ፣ በማዕድን ፣ በዲጂታል ፋይናንስ እና በሌሎችም ተጨባጭ ስኬቶች መመዝገባቸውን የጠቃቀሱት አቶ ሞገስ የኑሮ ውድነቱን ለማቃለል እና የስራ ዕድል አማራጮችን ለማስፋት የሚደረገውን አበረታች ርብርብ ማጠናከር እንደሚገባም አመላክተዋል።
ከለውጡ በፊት 30 ቢሊዮን ብር አካባቢ የነበረው የከተማችን ገቢ ባለፈው ዓመት 145 ቢሊዮን ብር ከመድረሱ በተጨማሪ 70 በመቶውን በጀት ለካፒታል ፕሮጀክቶች ማዋል በመቻሉ በአዲስ አበባ እንደ ሀገርም እየሰፉ የሚገኙ ኮሪደር ልማትን የመሳሰሉ አንፀባራቂ ድሎች እየተመዘገቡ መሆናቸውንም አቶ ሞገስ አስረድተዋል።
የትምህርት ተቋማት ለሀገራችን ሁለንተናዊ ዕድገት አበርክቷቸው ከፍ ያለ መሆኑን ያስገነዘቡት አቶ ሞገስ ትምህርትና ስልጠናን ፍትሀዊ ፣ አካታችና ተደራሽ በማድረግ ፣ ሁለንተናዊ ስብዕናቸው የተሟላ ዜጋ በማፍራት ፣ በትምህርት ለትውልድ ንቅናቄ የት/ቤቶችን አቅም በማሳደግ እና በሌሎችም አበረታች ውጤቶች መገኘታቸውን አብራርተዋል።
ጠንካራ የትምህርት ስልጠና ስርዓትንና የትምህርት ሴኩላሪዝምን በመተግበር በመልካም ስነምግባር የታነፁ ፣ በዕውቀት የተገነቡ ዜጎችን ለማፍራት እንዲሁም ቴክኖሎጂን ለማስፋፋት እና የማህበረሰብና የአካባቢ ልማት ለማጎልበት ዩኒቨርስቲው ሚናውን እንዲያጠናክር መምህራን ርብርባቸውን ሊያሳድጉ እንደሚገባም አቶ ሞገስ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
ጥልቅ ጥናትና ምርምር በማድረግ መፍትሄ አመንጪነትን በማሳደግ ፣ የትምህርት ጥራትን በማሳደግ ፣ በሀገሩ የማይደራደር ዜጋ በማፍራት የጋራ ብሔራዊ ተግባቦት ለመፍጠር መምህራን በአርአያነት ሊንቀሳቀሱ እንደሚገባም አሳስበዋል።
በህዝብ ድምፅ የመጣ መንግስት በመሆኑ በየጊዜው ህዝብን ማዳመጥ ፣ ብዥታዎችን ማጥራት ፣ ችግሮችን በጋራ የመፍታት ጥረቱ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አቶ ሞገስ ገልፀዋል።
የኮተቤ ትምህርት ዩኒቨርስቲ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ብርሃነመስቀል ጠና እንደ ሀገር በሁሉም ዩኒቨርስቲዎች እየተደረገ ያለው ውይይት ዓለም አቀፋዊ ፣ ቀጠናዊና ሀገራዊ ጉዳዮችን የጋራ በማድረግ በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ የተሟላ ዕይታ ለመፍጠር አጋዥ መሆኑን ጠቅሰዋል።
ስንነጋገር ፣ ስንወያይ ለችግሮች ሁሉ መፍትሄ እናመነጫለን ያሉት ዶ/ር ብርሃነመስቀል የጀመርነውን ሀገራዊ ለውጥ አጠናክሮ ለማስቀጠል ፣ ክፍተቶችን ለመሙላት ግብአት ስለሚገኝበት ከመሰል ውይይቶች ሀገር ትጠቀማለች ብለዋል።
የሚደነቀውን ማድነቅ ፣ ጉድለትን ደግሞ ማሳየት ጥቅሙ ለሀገርና ለህዝብ መሆኑን በመረዳት በመድረኩ መፍትሄንም ያመላከቱ ሀሳቦች መነሳታቸውን ጠቅሰዋል።
ሀገር የሚገነባው ተገቢውን መስዋዕትነት በመክፈል ከግል ፍላጎት ተሻግሮ ለህዝብ ዘላቂ ተጠቃሚነት እና ለሀገር ቀጣይነት ያለው ዕድገት በማሰብ ፣ የራስን አሻራም በማሳረፍ መሆኑን የጠቆሙት አስተያየት ሰጪዎች የከፍተኛ ትምህርት እና ምርምር ተቋማትና መምህራንም የሚጠበቅባቸውን ሊወጡ እንደሚገባ አስረድተዋል።
በየዘርፉ ተጨባጭ ውጤቶች መመዝገባቸውን የጠቀሱት የውይይቱ ተሳታፊ መምህራን የትምህርት ሴክተሩ የሀገር መሰረት በመሆኑ ኢንቨስት የማድረጉ ጥረት ሊጠናከር እንደሚገባም ገልፀዋል።
ከዩኒቨርሲቲው የሚፈልቁ ለሀገር ጠቃሚ ሀሳቦችን ተግባራዊ ማድረግ እንደሚገባ የጠቆሙት የውይይቱ ተሳታፊዎች የሀገሪቱ ኢኮኖሚ በፈቀደው መጠን የመምህራንን ህይወት ለማሻሻል እየተደረጉ የሚገኙ ጥረቶች ሊጠናከሩ እንደሚገባም ጠይቀዋል።
የኮተቤ ትምህርት ዩኒቨርስቲ በቅርቡ ከፍ ባለ መነቃቃት ላይ
መሆኑን የተናገሩት ተሳታፊዎቹ ለከተማዋ የሚያደርገውን ጥናትና ምርምር እንዲያጠናክር በከተማ አስተዳደሩ የሚደረግለት ድጋፍ ሊጠናከር እንደሚገባም አስረድተዋል።
Comments
ምንም አልተገኘም.
አስተያየቶችዎን ይተዉት.