
መምህራንን ጨምሮ በከተማ አስተዳደሩ የሚገኙ የመንግስት ሰራተኞችን በ25/75 ፕሮግራም የቤት ባለቤት
መምህራንን ጨምሮ በከተማ አስተዳደሩ የሚገኙ የመንግስት ሰራተኞችን በ25/75 ፕሮግራም የቤት ባለቤት ለማድረግ የሚያስችል የውል ስምምነት ፊርማ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዘዳንት አቶ አቤ ሳኖ እና በአዲስ አበባ ከተማ ቤቶች ልማትና አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ በወይዘሮ ቅድስት ወልደ ጊዮርጊስ አማካይነት ተካሄደ።
በስምምነት ፊርማ መርሀ ግብሩ የአዲስ አበባ ቤቶች ልማትና አስተዳደር ቢሮ ፣ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ እንዲሁም የአዲስ አበባ መምህራን ማህበር አመራሮችና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው አካላት የተገኙ ሲሆን በጉዳዩ ዙሪያ ለተለያዩ ሚዲያዎች ጋዜጣዊ መግለጫ ሰተዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ ቤቶች ልማትና አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ቅድስት ወልደ ጊዮርጊስ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በከተማ አስተዳደሩ ለሚገኙ ቤት ፈላጊ ሰራተኞች በዝቅተኛ የወለድ መጠን በ20 አመት የሚከፈል ብድር በማመቻቸቱ በከተማ አስተዳደሩ ስም ምስጋና አቅርበው ቀደም ሲል ተደራጅተው በመጠባበቅ ላይ የነበሩ ቤት ፈላጊ መምህራን በፕሮግራሙ ቅድሚያ የሚሰጣቸው መሆኑንም አመላክተዋል።
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዘዳንት አቶ አቤ ሳኖ በበኩላቸው ባንኩ በከተማ አስተዳደሩ ለሚገኙ እና ቤት ፈላጊ ለሆኑ የመንግስት ሰራተኞች 25% የሚሆነውን ገንዘብ መቆጠብ ለሚችሉ ሰራተኞች ብድር ለማቅረብ ዝግጅት ማድረጉን ገልጸው ከተማ አስተዳደሩም በፍጥነት መሬት ማቅረብ ከቻለ እና ሰራተኛውም የሚጠበቅበትን ገንዘብ በአግባቡ በመቆጠብ ዝግጁ ከሆነ ባንኩ ብድሩን ለመልቀቅ ዝግጁ መሆኑን በጋዜጣዊ መግለጫው አረጋግጠዋል።
ከተማ አስተዳደሩ ቤት ፈላጊ መምህራንን የቤት ባለቤት ለማድረግ ያላሰለሰ ጥረት ሲያደርግ መቆየቱን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ዘላለም ሙላቱ ገልጸው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በ25/75 መርሀ ግብር ለመምህራን ቅድሚያ በመስጠት በዝቅተኛ የወለድ መጠን ብድር በማመቻቸቱ ምስጋና አቅርበው ከተማ አስተዳደሩም ከሊዝ ነጻ የሆነ መሬት ለማቅረብ ዝግጅት ማጠናቀቁን አስታውቀዋል።
የዛሬው የስምምነት ፊርማ ከተማ አስተዳደሩ የመምህራንን ጥያቄ ለመመለስ ቁርጠኛ መሆኑን ያረጋገጠበትና ለአመታት በመምህራን ሲጠየቅ የቆየ ጥያቄ ምላሽ ያገኘበት መርሀግብር መሆኑን የአዲስ አበባ መምህራን ማህበር ፕሬዘዳንት አቶ ድንቃለም ቶሎ ሳ ጠቁመው ንግድ ባንክን ጨምሮ የመምህራንን ጥያቄ ምላሽ ለሰጡ አካላት ምስጋና አቅርበዋል።
Comments
ምንም አልተገኘም.
አስተያየቶችዎን ይተዉት.