
አዲስ አበባ በአስደማሚ የለውጥ ጎዳና ውስጥ ትገኛለች ። በመፍጠር እና በመፍጠን እየተገነቡ የሚገኙ ፕሮጀክቶች ከተማችን የቆየችበትን አዝጋሚ ዕድገት የሚያካክሱ ናቸው።
የህዝባችንን ፍትሀዊ ተጠቃሚነት እያረጋገጡ ፣ የከተማችንን ተምሳሌትነት ከፍ እያደረጉ የሚገኙ ግዙፍ ፕሮጀክቶች ይበልጥ እንዲሰፉ የህዝብ ግንኙነትና የሚዲያ ስራዎች ሚና ላቅ ያለ ነው፡፡
በከተማችን የሚኖሩ የሚዲያ ባለሙያዎችና አመራሮች ግዙፍና ሰው ተኮር ፕሮጀክቶችን ይበልጥ አውቀው እንዲያሳውቁ የሚያገዛቸውን ጉብኝት እያከናወኑ ይገኛሉ።
በሚዲያ ባለሙያዎች ከተጎበኙ ግዙፍ የልማት ፕሮጀክቶች መካከል የነገዋ የሴቶች የተሀድሶና የልህቀት ማዕከል አንዱ ነው።
ማዕከሉ በሴተኛ አዳሪነት እና በጎዳና ህይወት ውስጥ የቆዩ ፣ ከአስከፊ የውጭ ሀገር ቆይታ የተመለሱ እና አካል ጉዳተኛ ሴቶችን እየተቀበለ የስነልቦና እና የሙያ ስልጠና ፣ የህክምና ፣ የምኝታ ፣ የስፖርት ፣ የምገባ እና መሰል አገልግሎቶችን በተቀናጀና በተደራጀ መልኩ እየሰጠ እንደሚገኝ ተገልጿል።
በሁለት ዙሮች ብቁ ባለሙያዎችን በተለያዩ የስራ መስኮች አሰልጥኖ ወደ ስራ ያስገባው ይህ ማዕከል የከተማ ግብርና ስራዎችንም እያከናወነ ሲሆን ለተጨማሪ ገቢ ማስገኛ እየተገነባ የሚገኘው ተጨማሪ ህንፃም በመጠናቀቅ ላይ እንደሚገኝ መመልከት ተችሏል።
ሌላኛው የሰው ተኮር ፕሮጀክቶች ማሳያ የሆነው እና በአቃቂ ቃሊቲ ክ/ከተማ የሚገኘው የአይነ ስውራን አዳሪ ት/ቤትም ከሁሉም የሀገራችን አካባቢዎች የሚመጡ ተማሪዎችን ተቀብሎ እያስተማረ መሆኑን የጉበቱ ተሳታፊዎች ተመልክተዋል።
የሚዲያ ባለሙያዎች እና አመራሮች በሁለት ቡድን የከተማችንን ዋና ዋና ግዙፍ ፕሮጀክቶች እየጎበኙ ሲሆን በቅርቡ ተጨማሪ ድምቀት የሆነውን የካዛንችሽ እና አካባቢው ኮሪደር ልማት ፣ ነዋሪዎች ከስጋት ህይወት እያወጡ የከተማችንን ወንዞች ህልውና እየታደጉ የሚገኙትን የወንዝ ዳር ፕሮጀክቶች እና ሌሎችንም ሰው ተኮር ልማቶች እየጎበኙ ይገኛሉ።
Comments
ምንም አልተገኘም.
አስተያየቶችዎን ይተዉት.