
የ2017 ዓ/ም የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተናን አስመልክቶ የተዘጋጀ የጸጥታ ዕቅድ ቀርቦ ለጸጥታ እና ለትምህርት ተቋማት አመራሮች የስራ ስምሪትና መመሪያ ተሰጠ።
ሰኔ 13 ቀን 2017 ዓ/ም በአዲስ አበባ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ ሠላም አዳራሽ እቅዱን አስመልክቶ በተደረገው ውይይት ላይ የአዲስ አበባ ከተማ ሠላም እና ጸጥታ አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ሊዲያ ግርማ፣ የአዲስ አበባ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ጌቱ አርጋው፣ የከተማው የትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር ዘላለም ሙላቱ፣ የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ተጠባባቂ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ሳሙኤል ክፍሌ ጨምሮ ልዩ ልዩ የፀጥታና የትምህርት ተቋማት የስራ ኃላፊዎች የተገኙ ሲሆን የጋራ ፀጥታ መነሻ ዕቅድ ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል።
ተግባሩን በስኬት ለማጠናቀቅ አስፈላጊው ቅድመ ዝግጅት መደረጉን፤ ከባለፈው ጊዜ የተሻለ ስራ ሊሰራ እንደሚገባ እና የመፈተኛ ጣቢያዎችን ሠላማዊ ማድረግ ወሳኝ ስለመሆኑ እንዲሁም ስርቆትና ኩረጃን ለመከላከል በተለይ ፍተሻው በጥብቅ ዲሲፕሊን ሊመራ እንደሚገባ በመድረኩ ተገልጿል፡፡
በያዝነው ወር የ6ኛ እና የ8ኛ ክፍል ፈተናዎች በስኬት መጠናቀቃቸው የሚታወስ ሲሆን ለ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና በከተማ ደረጃ 112 የመፈተኛ ጣቢያዎች መኖራቸው የተገለፀ ሲሆን ፈተናው ፍጹም ሠላማዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ለማስቻል ታስቦ የጋራ እቅዱ የተዘጋጀ ሲሆን በእቅዱ መሰረት ሊሰራ እንደሚገባም መመሪያ ተሰጥቶበታል፤ አያይዘውም መላው የፀጥታ አካላት አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት አጠናቀው ወደ ስራ መገባቱም ተገልጿል ።
በአዲስ አበባ ከተማ በተዘጋጁት 112 የፈተና ጣቢያዎች ውስጥ በተፈጥሮ ሳይንስና በማህበራዊ ሳይንስ በአጠቃላይ 51.344 ተፈታኞች ለፈተና እንደሚቀመጡ ተገልጿል። የጸጥታ አካሉም ሆነ የትምህርት ማህበረሰቡ እንዲሁም የከተማችን ነዋሪዎች ፈተናው በሠላም እንዲጠናቀቅ ሁሉም ኃላፊነቱን ሊወጣ እንደሚገባ በመድረኩ መልዕክት ተላልፏል፡፡
በውይይቱ ላይ ከመድረኩ ተሳታፊዎች ለተነሱ ጥቆማዎችና አስተያየቶች መድረኩን በመሩት ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ማብራሪያ ተሰጥቶባቸዋል፡፡
Comments
ምንም አልተገኘም.
አስተያየቶችዎን ይተዉት.