በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በበይነ መረብ (...

image description
- ውስጥ Current Affairs    0

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በበይነ መረብ (online) የሚሰጠው የ2017 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ብሔራዊ ፈተና ተጀመረ ።

ፈተናው በከተማ አስተዳደሩ በ108 የማስፈተኛ ጣቢያዎች ሙሉ ለሙሉ በበይነ መረብ በመሰጠት ላይ የሚገኝ ሲሆን ፈተናው ስኬታማ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ቀደም ሲል ተማሪዎቹ የልምምድ ፈተና እንዲወስዱ መደረጉን እና በቂ ኦረንቴሽን መሰጠቱ እንዲሁም በየመፈተኛ ጣቢያው መሰረተ ልማቶቹን ዝግጁ የማድረግ ስራን ጨምሮ የተለያዩ የቅድመ ዝግጅት ስራዎች ሲሰሩ መቆየቱ ይታወቃል።

በዛሬው የመጀመሪያ ዙር ፈተና ከ13ሺ በላይ ተማሪዎች በ108 የመፈተኛ ጣቢያዎች ፈተናውን በበይነ መረብ በመውሰድ ላይ የሚገኙ ሲሆን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ዘላለም ሙላቱ ከኢፌድሪ ትምህርት ሚኒስቴር ዴታ ከወይዘሮ አየለች እሸቴ እና ከምክትል ቢሮ ኃላፊው አቶ ዲናኦል ጫላ ጋር በመሆን ፈተናው ከሚሰጥባቸው ጣቢያዎች መካከል አንዱ በሆነው አብረሆት ተገኝተው የፈተናውን አጀማመር በመመልከት ተማሪዎችን አበረታተዋል።

በከተማ አስተዳደሩ የ2017 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና በበይነ መረብ መሰጠቱ ተማሪዎቹ ፈተናውን በተረጋጋ ሁኔታ እንዲፈተኑ ከማስቻሉ ባሻገር ከኩረጃ ነጻ የሆነ የፈተና ስርአት እንዲሰፍን የሚያስችል መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ዘላለም ሙላቱ ጠቁመው ቢሮው ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር በጋራ በመሆን ፈተናው ስኬታማ ሆኖ እንዲጠናቀቅ በርካታ የቅድመ ዝግጅት ስራዎችን ሲሰራ መቆየቱን በመግለጽ ለተፈታኝ ተማሪዎች የመልካም ምኞት መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

በአዲስ አበባ ከተማ ከ280 አስፈታኝ ትምህርት ቤቶች የተውጣጡ 51,259 የተፈጥሮ እና የማህበራዊ ሳይንስ ተማሪዎች በአራት ዙር የ2017 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና እንደሚወስዱ ቀደም ሲል መገለጹ ይታወቃል።


Comments

ምንም አልተገኘም.

አስተያየቶችዎን ይተዉት.