ማሳሰቢያ ለአሽከርካሪዎች በመንገድ ግንባታ ላይ ያሉ በጊዜያዊነት ዝግ የሆኑ መንገዶች እና አማራጭ መንገዶችን ስለማሳወቅ:-
ከ4 ኪሎ እስከ ፒያሳ ባለው መስመር የራስ መኮንን ድልድይ እየተሰራ በመሆኑ የመንገድ ግንባታው እስኪጠናቀቅ ድረስ የትራፊክ መጨናነቅ እንዳይፈጠር ፍጹም መቆም የሚከለክሉ የትራፊክ ምልክቶች በመተከል ላይ ይገኛሉ::
እስከአሁን ባለው ሂደት በተለይም በስራ መግቢያ እና መውጫ ሰዓት በአካባቢው ላይ በመንገድ መዘጋጋት ህብረተሰቡ እንዳይጉላላ አሽከርካሪዎች ሌሎች አማራጭ መንገዶችን በመጠቀም ለትራፊክ ፖሊስ አባላት እና ለባለስልጣን መስሪያ ቤቱ የቁጥጥር ሰራተኞች ትዕዛዝ ተባባሪ እንዲሆኑ የግንዛቤ ማስጨበጥ ስራ በአካባቢው በስፋት ሲሰጥ ቆይቷል።
በዚሁ መሰረት ፍጹም መቆም የሚከለክሉ ምልክት የተተከለባቸው ከቴዎድሮስ አደባባይ ወደ ዓድዋ ድል መታሰቢያ የሚወስድ ዋና መንገድ እና የውስጥ ለውስጥ መንገዶች፣ ዓድዋ ድል መታሰቢያ ዙሪያ እንዲሁም ማዘጋጃ ዙሪያ ከመጋቢት 19/2016 ዓ.ም ጀምሮ ጥብቅ ቁጥጥር ይጀመራል።
በአካባቢው ላይ በግዜያዊነት ለተሽከርካሪ ማቆሚያ አገልግሎት የሚውል የዓድዋ ድል መታሰቢያ ሰርፌስ ፓርኪንግ አገልግሎት መስጠት ስለጀመረ አሽከርካሪዎች እንደ አማራጭ መጠቀም ይችላሉ። ሁሉም አሽከርካሪዎች በመንገድ ግንባታው ስራ በጊዜያዊነት ለተሽከርካሪዎች ዝግ የሆኑ መንገዶችን አውቃችሁ ሌሎች አማራጭ ልትጠቀሙ የሚገቡ መንገዶች:-
* ከራስ መኮንን ድልድይ ወደ ደጎል አደባባይ
* ከአራት ኪሎ ወደ ራስ መኮንን ድልድይ፣ አማራጭ መንገድ ከአራት ኪሎ-አባድር
* ከደጎል አደባባይ ትራፊክ መብራት ወደ 4 ኪሎ
* ከአራዳ ክፍለ ከተማ 4 ኪሎ አደባባይ
* ከቅ/ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን ወደ ራስ መኮንን ድልድይ
* ከደጃች ውቤ ወደ ራስ መኮንን ድልድይ
* ከአፍንጮ በር ወደ ራስ መኮንን ድልድይ
* ከባሻወልዴ ችሎት ወደ ራስ መኮንን ድልድይ እና ከቀበና ወደ ፒያሳ የሚመጡ አሽከርካሪዎች መንገዱ ግንባታ ላይ መሆኑን ተገንዝባችሁ ሌሎች አማራጭ መንገዶችን እንድትጠቀሙ፣ ለትራፊክ ፖሊስ አባላት እና የቁጥጥር ሰራተኞች ትዕዛዝ እንደወትሮው ተባባሪ እንድትሆኑ እናሳውቃለን፡፡
በአካባቢው ያለውን የትራፊክ ፍሰት መጨናነቅን ለመቅረፍ አማራጭ ማስተንፈሻ የሚሆን መንገድ በተለምዶ ስሙ ከቀይባህር ኮንደሚንየም ወደ ደጎል አደባባይ የሚወስደው መንገድ ዛሬ ከሰዓት ለተሽከርካሪዎች ክፍት የሚሆን መሆኑን እናሳውቃለን።
Comments
ምንም አልተገኘም.
አስተያየቶችዎን ይተዉት.