በኮሪደር ልማቱ ቅርስ እና ታሪክ እየጠፋ ነው በሚል የሚሰራጨው መረጃ ሐሰት መሆኑን ከንቲባ አዳነች አቤቤ ተናገሩ
በኮሪደር ልማቱ ቅርስ እና ታሪክ እየጠፋ ነው በሚል የሚሰራጨው መረጃ ሐሰት መሆኑን የአዲስ አበባ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ተናግረዋል፡፡
ከንቲባዋ የኮሪደር ልማቱን አስመልክቶ ከመገናኛ ብዙሃን ለተነሱላቸው ጥያቄዎች ምላሽ እና ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
የኮሪደር ልማቱ ዋነኛ አላማ አዲስ አበባን እንደ ስሟ አበባ እና ውብ ማድረግ መሆኑን ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገልጸዋል፡፡
ልማቱ የሚያካልላቸው አካባቢዎችም የቀድሞ አሻራቸው ሳይጠፋ እየለሙ እና እየታደሱ መሆናቸውን አበክረዋል፡፡
በፒያሳ አካባቢ የሚገኙ በቅርስነት የተመዘገቡ ህንጻዎችም ታሪካቸው ተጠብቆ ይበልጥ ሳቢ እንዲሆኑ እየተሰራ መሆኑንም አብራርተዋል፡፡
ከንቲባዋ የአፍሪካ ህብረትን ጨምሮ የበርካታ ዓለም አቀፍ ተቋማት መቀመጫ የሆነችውን አዲስ አበባን ምቹ እና ዘመናዊ ለማድግ እየተሰሩ ያሉ ስራዎችን በቅንነት ባለማየት እየተሰነዘሩ ባሉ ትችቶች የከተማ አስተዳደሩ ቅር እንደማይሰኝም አመላክተዋል፡፡
በኮሪደር ልማቱ ከመኖሪያ አካባቢያቸው የተነሱ ዜጎች ምንም አይነት እንግልት እንዳይገጥማቸው አግባብነት ያለው ምትክ ቦታ እና ሌሎች ማካካሻዎች የተሰጣቸው መሆኑን እና ቅሬታ ያላቸው ወገኖችን የሚያስተዳናግድ ግብረሃይል በከንቲባ ጽ/ቤት ተደራጅቶ ሳምንቱን ሙሉ ከጠዋት እስከ ምሽት በመስራት ላይ መሆኑንም አስታውቋል፡፡
ልማቱ የከተማዋን አስፋፈር እና የሰፈር ሰያሜን ለመቀየር ያለመ ስለመሆኑ ስለሚናፈሰው መረጃ ሀሳባቸውን የተጠየቁት ከንቲባ አዳነች አቤቤ፤ የሚቀየር ስም አለመኖሩን ገልጸው ነገር ግን የሚታነቅ ዶሮ በከንቱ እሪ የሚባልበት ሰፈር ብሎም ውቤ በረሃ የሚሉ ስሞች የደረስንበትን ዕድገት የሚያመላከቱ አይደሉም ብለዋል፡፡
ፕሮጀክቱ ካለዉ ስፋት አንፃር በፒያሳ እና አራት ኪሎ ብሎም ሜክሲክ፣ ቦሌ መስመር የመንገድ ሰራውን እና አረንጋዴ ልማቱን እስከ ግንቦት መጨረሻ ለማጠናቀቅ እየተሰራ መሆኑንም አመላክተዋል፡፡
በልማት ስራው ሳቢያ የተፈጠረውን የትራፊክ መጨናነቅ ለመቀነስም ለአሽከርካሪዎች ተለዋጭ መንገዶች እንደሚሰራም ገልጸዋል፡፡
ከመንገድ ልማቱ ባሻገር በተለይ ልማቱ በሚያልፍባቸው መስመሮች ለሚሰሩ ትልልቅ ፕሮጀክቶች ግልጽ ጨረታ ይወጣልም ብለዋል፡፡
ወይዘሮ አዳነች አቤቤ የከተማዋ ነዋሪዎች ለመዲናዋ ልማት ላሳዩት ድጋፍ እና ትብብርም ምስጋናቸውን አቅርበው ለቀጣይ የመዲናዋ ልማትም ትዕግስታቸው እንዲቀጥል ጠይቀዋል፡፡
EBC
Comments
ምንም አልተገኘም.
አስተያየቶችዎን ይተዉት.