መንግሥት በአማራ እና በኦሮሚያ ክልሎች ሰላም ለማስፈን የተቀናጀ ርምጃ በመውሰዱ ክልሎቹ ወደ አንጻራዊ ሰላም ተመልሰዋል፡- የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት
መንግሥት በአማራ እና በኦሮሚያ ክልሎች ሰላም ለማስፈን የተቀናጀ ርምጃ በመውሰዱ ክልሎቹ ወደ አንጻራዊ ሰላም እና መረጋጋት መመለሳቸውን የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትሩ ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር) ገለጹ።
ሚኒስትሩ በዛሬው ዕለት በሰጡት መግለጫ፣ መንግሥት ያሉ ችግሮችን በሰላም እና በድርድር ለመፍታት ምንጊዜም ዝግጁ የነበረ ቢሆንም የሰላም አማራጩ ተቀባይነት በማጣቱ ሕግ በሚፈቅድለት አግባብ ሕግ ወደ ማስከበር ርምጃ ገብቶ ሲሠራ መቆየቱን ሚነስትሩ ገልጸዋል።
በዚህም መሠረት በአብዛኞቹ የአገሪቱ አካባቢዎች አንጻራዊ ሰላም እና መረጋጋት መፈጠሩን ጠቁመው፣ ይህንንም ይበልጥ ማጽናት ይገባል ብለዋል።
በአማራ ክልል የተጀመረው ሕግ የማስከበር ሥራ ውጤታማነቱን ጠብቆ እየቀጠለ መሆኑን ያስረዱት ዶክተር ለገሰ፣ በክልሉ ሕግ የማስከበር ርምጃውን ተከትሎ ክልሉ ከሞላ ጎደል ወደ ሰላም እና መረጋጋት የመጣበት ሁኔታ ተፈጥሯ ብለዋል።
ክልሉን መልሶ የማደራጀት እና አቅሙን የመገንባት ሥራ እየተሠራ ስለመሆኑም ጠቅሰዋል።
የክልሉን የጸጥታ ኃይል መልሶ በማደራጀት እና ሥልጠና በመስጠት የክልሉን ሰላም ለማስጠበቅ እየተሠራ ነው ብለዋል።
በአደናጋሪ መረጃ ተወናብደው የነበሩ ከ12 ሺህ በላይ ግለሰቦች የቀረበላቸውን የሰላም ጥሪ ተቀብለው ተሃድሶ ወስደው ከኅብረተሰቡ ጋር በመቀላቀል ሰላማዊ ኑሮ መጀመራቸውንም አንሥተዋል።
በልዩ ልዩ ምክንያ አኩርፈው እና ተበትነው የነበሩ ከ10 ሺህ በላይ የቀድሞ የክሉሉ ልዩ ኃይል አባላት በተደረገላቸው ጥሪ መሠረት ተሃድሶ ወስደው የክልሉን ሰላም ለመጠበቅ የበኩላቸውን ሚና እየተወጡ መሆናቸውን አስረድተዋል።
የክልሉ አመራር የሕዝቡን ሰላም እና ጥያቄ ለመመለስ እየሠራ እንደሚገኝም ሚኒስትሩ ተናግረዋል።
ጽንፈኛ ኃይሉ አሁን ላይ በየመንደሩ እና ሰፈሩ በመሰማራት መንገድ በመዝጋት በዘረፋ ወንጀል ላይ መሰማራቱን የገለጹት ሚኒስትሩ፣ ይህ ኃይል የክልሉ አርሶ አደር ማዳበሪያ ጭምር እንዳይደርሰው እያደረገ ነው ብለዋል።
በኦሮሚያ ክልል በሚንቀሳቀሰው የአሸባሪው ሸኔ ቡድን ላይም እየተወሰደ ያለው ርምጃ ተጠናክሮ መቀጠሉን ያነሱት ዶክተር ለገሰ፣ የሽብር ቡድኑ በሚንቀሳቀስባቸው አካባቢዎች ላይ መከላከያ ሠራዊት በወሰደው መጠነ ሰፊ ርምጃ ውጤት መገኘቱን አውስተዋል።
የመከላከያ ሠራዊት አሸባሪው ቡድን ሲጠቀምባቸው የነበሩ ዋሻዎች፣ ጫካ እና የተለያዩ ይዞታዎች መቆጣጠሩን ተናግረዋል።
በመሆኑም አሁን ላይ አሻባሪው ቡድን ይንቀሳቀስባቸው በነበሩ አካባቢዎች የሰላሙ ሁኔታ እየጎለበተ መምጣቱንም አስረድተዋል።
በዚህም የኦሮሚያ ክልል ለልማት እና ለመልካም አስተዳደር ሥራ የተመቸ እንዲሆን ተደርጓል ብለዋል።
ተፈናቃዮች ወደ ቀዬአቸው እንዲመለሱ የማድረግ ምቹ ሁኔታ መፈጠሩን ያነሱት ሚኒስትሩ፣ ይህም በአማራ እና በኦሮሚያ ክልል መንግሥታት የተቀናጀ ጥረት እየተከናወነ መሆኑን አውስተዋል።
ሰሞኑን በኦሮሚያ ክልል የተካሄዱ የድጋፍ ሰልፎች ሕዝቡ ለመረጠው መንግሥት፣ ለተገኙ ውጤቶች እና የልማት ትሩፋቶች ቀጣይነት ድጋፉን እና ዝግጁነቱን የገለጸበት እንደነበር ሚኒስትሩ ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር) በመግለጫቸው አንሥተዋል።
Comments
ምንም አልተገኘም.
አስተያየቶችዎን ይተዉት.