ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የኮሪደር ልማትን...

image description
- ውስጥ Current Affairs    0

ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የኮሪደር ልማትን አስመልክቶ የተሰጠ ጋዜጣዊ መግለጫ::

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በምርጫ ወቅት “ አዲስ አበባን እንደስሟ ውብ አበባ ለማድረግ እና ለነዋሪዎቿ ምቹ ” እንድትሆን ለመስራት ለህዝቡ ቃል በገባው መሰረት አዳዲስ መሰረተ ልማቶችን አቅዶ በመስራት እና ነባሮቹን በማደስ ሌት ተቀን እየሰራ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ከተማዋ ካለባት የመሰረተ ልማት እጥረት እና የህዝብ ቁጥር መጨመር ጋር ተያይዞ እንዲሁም ዘመናት ያስቆጠሩ መሰረተ ልማቶችን ለማዘመን፣ ለማደስ እና የነዋሪዎችን ፍትሀዊ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ የኮሪደር ልማት ማከናወን መጀመሩ ይታወቃል፡፡

ከዚህ ጋር ተያይዞ የከተማ ነዋሪዎች የአኗኗር ዘይቤ ለማሻሻል እና ከተማዋን የሚመጥን፤ ዘመኑን የሚዋጅ፤ የመሰረተ ልማት አቅርቦት ለመጨመር የተጀመረው የኮሪደር ልማት ስራ በጥናት ላይ ተመርኩዞ ቅድመ ዝግጅት ተደርጎ የተጀመረው ስራ በመገባደድ ሂደት ላይ ይገኛል፡፡ በዚህ ሂደት ከቅድመ ዝግጅት ጀምሮ እስከ ትግበራ ከማህበረሰቡ ጋር በመወያየት፣ በመግባባት እና በትብብር እያከናወንን እንገኛለን፡፡

በኮሪደር ልማትና በመልሶ ማልማት የሚነሱ የከተማችን ነዋሪዎችም የተሻለ መኖሪያ ቤት፣ ምትክ መሬት፣ ካሣ፣ የመስሪያ ቦታ፣ ሼዶች፣ የትራንስፖርት ወጪ፣ የሞራል ካሣ በቦታቸው በኮሪደር ልማቱ ጥናት መሰረት ማልማት ለሚችሉ መልሶ የማልማት መብት ተጠብቆላቸው እና ለግል የመኖሪያ ቤት ተነሺዎች እስከሚገነቡ የቤት ኪራይ ወጪ ጭምር እንዲያገኙ በማድረግ የተተገበረ ነው፡፡

ይህ በእንዲህ እያለ ሕዝቡን በተዛባ መረጃና ማስረጃ ማጭበርበር የሚፈልጉ እና የስነ ምግባር ጉድለት ያለባቸው አንዳንድ ሰዎች፤ በግልፅ ተወስኖ ከተነገረው ከአምስቱ የኮሪደር ልማት አካባቢዎች ውጪ በሌሎች አካባቢዎችም የኮሪደር ልማት ነው በማለት የልማት ተነሺዎች እንዳሉ አስመስለው የተዛባ መረጃ በማሰራጨት ህዝቡን ለማደናገር እየሞከሩ እንደሆነ ደርሰንበታል፡፡

በዚህ መሰረት የተወሰኑ ግለሰቦች ተይዘው ተጠያቂ የተደረጉ በመሆኑ፤ በኮሪደር ልማት ተወያይተው ምትክ ቦታ፣ ካሣ፣ ቤቶች እና ሌሎች ወጪዎች እየሰጠን ካስነሳናቸው ነዋሪዎች ውጪ ምንም ዓይነት የኮሪደር ልማት ተነሺ እንደሌለን ለማሳወቅ እንወዳለን፡፡

በመሆኑም የከተማችን ነዋሪዎች በግልፅ መድረክ ተፈጥሮ ውይይት ተደርጐ ስምምነት ከተደረሰባቸው አምስቱ የኮሪደር ልማት ቦታዎች ውጪ፣ ውዥንብር የሚፈጥሩ ሰዎችና አካላትን በከተማ አስተዳደሩ ጥቆማና በቅሬታ ማቅረቢያ ነፃ ስልክ ቁጥር 9977 እንድትጠቁሙ፣ እንዲሁም በከንቲባ ጽ/ቤት ለተቋቋመው የቅሬታ ሰሚ ኮሚቴ በአካል በመቅረብ እንድታሳውቁ እየገለፅን፤ ከዚህ ባለፈ የከተማችን ነዋሪዎች አሁን እየተሰራ ያለውን የልማት ስራ ለመስራት ሲባል የተፈጠረውን መጠነኛ እና ጊዜያዊ ውጣ ውረድ በመታገስና በመተባበር አብረን መስራታችንን እንድንቀጥል በአክብሮት እንጠይቃለን፡፡ 

እኛም ቃላችንን ጠብቀን ሌትና ቀን በመስራት “አዲስ አበባን እንደ ስሟ ውብ አበባ” ለነዋሪዎቿ ምቹ በማድረግ እንክሳችኋለን፡፡


Comments

ምንም አልተገኘም.

አስተያየቶችዎን ይተዉት.