በመዲናዋ የኢኮኖሚ ድርጅቶች ቆጠራ በይፋ ተጀመረ...

image description
- ውስጥ Current Affairs    0

በመዲናዋ የኢኮኖሚ ድርጅቶች ቆጠራ በይፋ ተጀመረ፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የኢኮኖሚ ድርጅቶች ቆጠራ በይፋ መጀመሩን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፕላንና ልማት ቢሮ አስታውቋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፕላንና ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ አደም ኑሪ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ቆጠራው የከተማችን እና የሀገራችንን ጥቅል ኢኮኖሚ ዕድገት ከዓለም ኢኮኖሚ  ጋር በማነፃፀር ደረጃውን ከማወቅ ባሻገር የግል አልሚዎች የኢንቨስትመንት አማራጮችን ለመጠቆም  ያግዛል ብለዋል፡፡

ቆጠራው የአገልግሎት፣ የኢንዱስትሪና የከተማ ግብርና የኢኮኖሚ ዘርፎች ለአጠቃላይ የሀገር ምጣኔ ሀብት ያላቸዉን   አበርክትዎ (GDP) ለማወቅና የዘርፎች የተናጠል ድርሻን ወቅታዊ ለማድረግ የሚረዳ ስታቲስቲካላዊ መረጃ  ለማግኘት፤ ብሎም በቀጣይነት ለሚከናወኑ ዘርፈ ብዙ ጥናቶችና ለፖሊሲዎች ግብዓት የሚሆን የተሟላ  መረጃ ለማግኘት እንደሆነም አቶ አደም ተናግረዋል፡፡

ቆጠራው በዲጂታል ዘዴ በ11ዱም ክፍለ ከተሞች 19 የሚሆኑ የኢኮኖሚ ዘርፎችን መሰረት አድርጎ ከጥቃቅን የንግድ ዘርፎች እስከ ባለ 5 ኮከብ ሆቴሎች ድረስ እንደ ሚካሄድም ኃላፊዉ በመግለጫቸው ተናግረዋል፡፡ 

የአዲስ አበባ ስታትስቲክስ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ተሠማ ኡርጌሳ በበኩላቸው በአጠቃላይ ቆጠራውን እንዲያከናዉኑ 5,653 መረጃ ሰብሳቢ፣ተቆጣጣሪ፣ ስታቲስቲሽያኖች እና አስተባባሪ ሰራተኞች በሁሉም ክፍለ ከተሞች ሥር በሚገኙ ወረዳዎች ተመድበዋል ብለዋል፡፡

ሁሉም የኢኮኖሚ ድርጅቶች፣ የከተማችን ነዋሪዎችና የብሎክ አደረጃጀቶች ትክክለኛ መረጃዎችን እንዲሰጡ በመተባበርና በማስተባበር ከማገዝ ባሻገር ጥናቱን ማወክ ከከተማ አስተዳደሩ ሆነ ከሀገሪቱ ፍላጎት ተፃራሪ መሆኑን አውቀው ከወዲሁ ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ ሲሉም አቶ አደም ኑሪ አሳስበዋል፡፡   
                                                                      ቆጠራው የተጀመረ ሲሆን የመጀመሪያው ምዕራፍ ቆጠራ ከጥቅምት 1 ቀን 2018 ዓ.ም ተጀምሮ ባሉት ተከታታይ 45 ቀናት ውስጥ ይጠናቀቃል፡፡

በተመሳሳይ ሁለተኛው ምዕራፍ ቆጠራ ደግሞ 1ኛው ዙር ከተጠናቀቀበት ቀን ጀምሮ በዋና ዋና የኢኮኖሚ ዘርፎች በየድርጅቶቹ አድራሻ በመገኘት እስከ የካቲት 30 ቀን 2018 ዓ.ም ባሉት ቀናት መረጃው ተሰብስቦ እንደሚጠናቀቅም ተገልጿል፡፡


Comments

ምንም አልተገኘም.

አስተያየቶችዎን ይተዉት.