"ዘመኑን የዋጀ የመረጃ ፍሰትን የመፍጠርና በመንግስት እና በህዝብ መካከል ያለውን ግንኙነት የማጠናከር ስራዎች በሌሎችም ክፍለ ከተሞች ማስፋት ይገባል፡፡ አቶ ሀፍታይ ገ/እግዚያብሔር
የየካ ክፍለ ከተማ አስተዳደር ኮሙኒኬሽን ጽ/ቤት ዘመናዊ የሚዲያ ስቱዲዮ፣ የተሻሻለ ዌብሳይት እና የመረጃ ማዕከል በዛሬዉ እለት በይፋ ተመርቆ አገልግሎት መጀመሩ ተገልጿል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ኮሙኒኬሽን ቢሮ ሀላፊ አቶ ሀፍታይ ገ/እግዚያብሔር፣ የየካ ክፍለ ከተማ አስተዳደረ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ፍጹም ኃይሌን ጨምሮ የክፍለ ከተማው አስተባባሪ ኮሚቴ እና የሌሎች ክ/ከተሞች ኮሙኒኬሽን ሀላፊዎች በምርቃት ስነስርዓቱ ላይ ተገኝተዋል፡፡
መንግስትና ህዝቡን በቀጥታ የሚያገናኝ የመገናኛ ብዙሃን አውታር በመፍጠር ፈጣን እና ቀልጣፋ የመረጃ ልውውጥ ለማድረግ ትልቅ ሚና ያለዉ መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ አሰትዳር ኮሙኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ ሀፍታይ ገ/እግዚዓብሔር ተናግረዋል።
የየካ ክፍለ ከተማ ኮሙኒኬሽን ፅህፈት ቤት እየተገበረ ያለዉን ዘመኑን የዋጀ የመረጃ ፍሰትን የመፍጠርና በመንግስት እና በህዝብ መካከል ያለውን ግንኙነት የማጠናከር ስራዎች በሌሎችም ክፍለ ከተሞች ማስፋት ይገባልም ብለዋል፡፡
በተጨማሪም በዘመናዊ መንገድ የተደራጀውና አገልግሎት መስጠት የጀመረው ዌብሳይት (yekacommunication.gov.et) የክፍለ ከተማውን አስተዳደር መዋቅር፣ አገልግሎቶች፣ ዜናዎችና ማስታወቂያዎችን በቀላሉ ተደራሽ የሚያደርግ አዲስ ምእራፍ የከፈተ ነዉ በማለት ገልፀዋል።
የከተማ አስተዳደሩ መረጃ ወጥነት ባለው መልኩ ተደራሽ እንዲሆን የየካ ክፍለ ከተማ አስተዳደር ላደረገው አስተዋፅኦ
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ኮሙኒኬሽን ቢሮ ሀላፊ አቶ ሀፍታይ ገ/እግዚያብሔር ምስጋና አቅርበዋል።
የየካ ከፍለ ከተማ አስተዳደር ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ፍጹም ኃይሌ በበኩላቸው አዲሱ ስቱዲዮና ዌብሳይት የክፍለ ከተማውን የአገልግሎት አሰጣጥ ከማሻሻል ባሻገር በህዝብና በመንግስት መካከል ያለውን የመረጃ ክፍተት በማጥበብ ለክፍለ ከተማው እድገትና ብልጽግና የበኩሉን አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።
ዌብሳይቱ የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን፣ ቅሬታዎችንና ጥቆማዎችን በአስተማማኝ ሁኔታ ለመቀበል የሚያስችል የመረጃ ማስገቢያ ቅጽ ያለው ሲሆን ይህም የአስተዳደሩን ግልጽነትና ተጠያቂነት ለማጠናከር ያለመ መሆኑን ተናግረዋል፡፡።
አዲሶቹ የመገናኛ ዘዴዎች የክፍለ ከተማውን የእለት ተእለት እንቅስቃሴ፣ ውይይቶች እና የነዋሪዎችን ተሳትፎ የሚያንጸባርቁ የተለያዩ የኦዲዮ፣ የቪዲዮ እና የጽሑፍ ይዘቶችን በየጊዜው በማዘጋጀት ለህዝብ እንደሚያደርሱ የየካ ክፍለ ከተማ ኮሙኒኬሽን ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ታደለ በቀለ ቃል ገብተዋል።
የክፍለ ከተማውን የመልካም አስተዳደር፣ የልማት ስራዎች እና የአገልግሎት አሰጣጥ በተመለከተ ወቅታዊ፣ ትክክለኛና ጥራት ያለው መረጃ ለነዋሪዎች በቀጥታ ለማድረስ የሚያስችል ዘመናዊ የቴክኖሎጂ አቅም የተገጠመለት መሆኑ ጭምር ተገልጿል።
Comments
ምንም አልተገኘም.
አስተያየቶችዎን ይተዉት.