29ኛ መደበኛ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ስብሰባ ው...

image description
- ውስጥ Current Affairs    0

29ኛ መደበኛ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ስብሰባ ውሳኔዎች የሚኒስትሮች ምክር ቤት በዛሬው ዕለት ባካሄደው 29ኛ መደበኛ ስብሰባ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አሳልፏል፡፡

1. ምክር ቤቱ በቅድሚያ የተወያየው በመንግስት የአገልግሎትና አስተዳደር ረቂቅ ፖሊሲ ላይ ነው፡፡ መንግስት የሚያወጣቸውን ህጎች፣ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች በመፈጸምና በማስፈጸም እንዲሁም የሀገረ መንግስት ግንባታ ሂደቱን በማፋጠን ረገድ የመንግሥት አገልግሎትና አስተዳደር ተቋማት ሚና የጎላ ነው፡፡ በዚህም መሰረት ፖሊሲው ሊፈታቸው እና በቀጣይ ሊሰራባቸው የሚገቡ ጉዳዮች በ7 ዋና ዋና ምሰሶዎች መሰረት በማድረግ ተዘጋጅቶ ቀርቧል፡፡ እነዚህም ነፃና ገለልተኛ የሲቪል ሰርቪስ መገንባት ፤ብዝኃነትና አካታችነትን ያረጋገጠ ሲቪል ሰርቪስ ግንባታን ማፋጠን፤ የመንግሥት አደረጃጀትና አስተዳደር ሥርዓትን ማሳለጥ፤ ቀልጣፋና ተደራሽ የመንግሥት አገልግሎት አቅርቦት ሥርዓት መዘርጋት፤ የመንግሥት ሠራተኞች የብቃት ማረጋገጫ ሥርዓት መገንባትና የማስፈጸም ዐቅምን ማሳደግ፤ የዲጂታል ሲቪል ሰርቪስ በመገንባት ቅቡልነት ያላቸው አገልግሎቶችንና ውሳኔዎችን ማቀላጠፍ፤ የሲቪል ሰርቪስ ገቢር ነበብነት (Pragmaticism) አመራር እና ተቋም ግንባታን ማፋጠን ናቸው፡፡ ምክር ቤቱም በረቂቅ ፖሊሲው ላይ ተወያይቶ ግብዓቶችን በማከል በስራ ላይ እንዲውል በሙሉ ድምጽ ወስኗል፡፡

2. በመቀጠል ምክር ቤቱ የተወያየው የጥቃቅን፣ አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ልማት ረቂቅ ፖሊሲ ነው፡፡ ፖሊሲው ለጥቃቅን፣ አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ምስረታ፣ እድገትና መስፋፋት ምቹ ሁኔታ በመፍጠር፣ ለዘርፉ የሚሰጡ ድጋፎች ፍላጎትን እና አቅምን ያገናዘቡ እንዲሆኑ በማድረግ፣ ኢመደበኛ የንግድ ስራዎችን በመደገፍ የዘርፉ ልማት አካታች እንዲሆን በማድረግ በኢኮኖሚው ላይ የሚኖረውን በጎ አስተዋፅዖ ከፍ ለማድረግ የሚያስችል ሆኖ ቀርቧል፡፡ ምክር ቤቱም በረቂቅ ፖሊሲው ላይ ከተወያያ በኋላ ግብዓቶችን በማከል በስራ ላይ እንዲውል በሙሉ ድምጽ ወስኗል፡፡

3. በሶስተኛነት ምክር ቤቱ የተወያየው የአካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣንን አደረጃጀት፣ ስልጣንና ተግባርን ለመወሰን በቀረበው ረቂቅ ደንብ ላይ ነው፡፡ ባለስልጣኑ አንድ ተቆጣጣሪ ተቋም ሊያከናውናቸው የሚገባቸውን ተግባራት በብቃት መፈጸም እንዲችል፣ በስራ ላይ ያሉ የአካባቢ ጥበቃ ፖሊሲዎች፣ ህጎች እና ደረጃዎች እንዲሁም ኢትዮጵያ የተቀበለቻቸው አለም አቀፍ የአካባቢ ጥበቃ ስምምነቶችን መተግበር እና ማስተግበር እንድትችል የባለስልጣኑን ስልጣንና ተግባር እንዲሁም አደረጃጀት የሚወስን ረቂቅ ሆኖ ለምክር ቤቱ ቀርቧል፡፡ ምክር ቤቱም በረቂቅ ደንቡ ላይ ከተወያየበት በኋላ ግብአቶችን በማከል በነጋሪት ጋዜጣ ታትሞ ከወጣበት ቀን ጀምሮ በስራ ላይ እንዲውል በሙሉ ድምጽ ወስኗል፡፡

4. ምክር ቤቱ በአራተኛነት የተወያየው የኢትዮጵያ ደረጃዎች ረቂቅ አዋጅ ላይ ነው፡፡ ረቂቅ አዋጁ በሀገር ውስጥ የሚመረቱ፣ ወደ ሀገር የሚገቡ እና ወደ ውጪ የሚላኩ ምርቶች፣ አገልግሎቶች እና ሂደቶች የጥራት ደረጃቸውን የጠበቁ እና ደረጃ የወጣላቸው እንዲሆኑ፣ ይህም በመላው አገሪቱ እንዲተገበር የሚያስችል፣ በተቆጣጣሪ አካላት መካከል ቅንጅታዊ አሰራር እንዲኖር፣ ግልጽነትና ተጠያቂነት እንዲሰፍን የሚያስችል ረቂቅ ለምክር ቤቱ ቀርቧል፡፡ ምክር ቤቱም በረቂቅ አዋጁ ላይ ከተወያየ በኋላ ግብዓቶችን በማከል ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፍ በሙሉ ድምጽ ወስኗል፡፡

5. የሕጋዊ ሥነ-ልክ ረቂቅ አዋጅ ምክር ቤቱ የተወያየበት አምስተኛ አጀንዳ ሲሆን ከንግድ ልውውጥ፣ ከጤና፣ ከደህንነት እና ከአካባቢ ጥበቃ ጋር በተያያዘ አገልግሎት ላይ የሚውሉ ልኬቶችንና የመለኪያ መሣሪያዎችን ትክክለኛነት በማረጋገጥ የሰውን እና የእንስሳትን ጤንነትና ደህንነት ማስጠበቅ እንዲሁም የአካባቢ ብክለትን መከላከል ለሁለንተናዊ ብልጽግና መሰረቶች በመሆናቸው፣ ከአለም አቀፍ የሕጋዊ ሥነ-ልክ ህግጋት ጋር የተጣጣመ ህግ በማውጣት አለም አቀፍ የንግድ ትስስራችን ለማጎልበት የላቀ ጠቀሜታ ያለው ረቂቅ አዋጅ ለምክር ቤቱ ቀርቧል፡፡ ምክር ቤቱም ረቂቅ አዋጁ ላይ ከተወያየ በኋላ ግብዓቶችን በማከል ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፍ በሙሉ ድምጽ ወስኗል፡፡

6. የኢትዮጵያ ሥነ-ልክ ኢንስቲትዩትን ለማቋቋም የቀረበ ረቂቅ ደንብ በሥነ-ልክ፣ በካሊብሬሽንና በሳይንስ መሳሪያ ዘርፍ አለም ከደረሰበት የቴክኖሎጂ እድገት ጋር የሚጣጣም አገልግሎት መስጠት እንዲችል፣ የጥናትና ምርምር፣ የማማከር እና የስልጠና ስራዎችን ማከናወን የሚያስችለው ረቂቅ ደንብ ሆኖ ቀርቧል፡፡

7. የኢትዮጵያ ብሔራዊ አክሬዲቴሽን ጽሕፈት ቤትን ለማቋቋም የቀረበ ረቂቅ ደንብ ዓለም አቀፍ ተቀባይነት ያለው ብሔራዊ የአክሬዲቴሽን ስርዓት በመገንባት የሀገር ውስጥና የውጪ ንግድ እንዲቀላጠፍ፣ የሕብረተሰቡ ጤናና ተጠቃሚነት እንዲሁም የአካባቢ ደህንነት እንዲጠበቅ ብሎም ፍትሐዊ የግብይት ስርዓት እንዲሰፍን በሚያስችል መልኩ ተቋሙን የሚያጠናክር ረቂቅ ደንብ ህኖ ለምክር ቤቱ ቀርቧል፡፡

8. የኢትዮጵያ የተስማሚነት ምዘና ድርጅትን እንደገና ለማቋቋም የቀረበው ረቂቅ ደንብም በሀገር ውስጥ የሚመረቱም ሆነ ወደ ሀገር የሚገቡ ምርቶችና አገልግሎቶች ዓለም አቀፍ ደረጃዎችን እና ሕጋዊ መስፈርቶችን ማሟላታቸውን በኢንስፔክሽን፣ በሰርተፊኬሽን እና በፍተሻ ላብራቶሪዎች በማረጋገጥ የተጠቃሚውን ህብረተሰብ ጤና እንዲጠበቅ ማድረግ ይቻለው ዘንድ ረቂቅ ደንብ ቀርቧል፡፡

ምክር ቤቱም እላይ የተጠቀሱትን ሶስቱ ረቂቅ ደንቦች ላይ ከተወያየ በኋላ ግብአቶችን በማከል በነጋሪት ጋዜጣ ታትመው ከወጡበት ቀን ጀምሮ በስራ ላይ እንዲውሉ በሙሉ ድምጽ ወስኗል፡፡

9. በመጨረሻም ምክር ቤቱ የስደተኞችና ተመላሾች አገልግሎት አደረጃጀት፣ ስልጣንና ተግባር ለመወሰን በቀረቡ ረቂቅ ደንብ ላይ ተወያይቷል፡፡ ለስደተኞች እና ተመላሾች ተገቢውን ጥበቃ ማድረግ እንዲቻል፣ ኢትዮጵያ ያጸደቀቻቸውን ዓለም አለም አቀፍ እና አህጉራዊ ስምምነቶች በአግባቡ በመተግበር ስደተኞች ከለላና ድጋፍ እንዲያገኙ ተቋሙ ሚናውን በአግባቡ እንዲወጣ የሚያስችለው ረቂቅ ደንብ ለምክር ቤቱ ቀርቧል፡፡ ምክር ቤቱም በረቂቅ ደንቡ ላይ ከተወያየ በኋላ ግብአቶችን በማከል በነጋሪት ጋዜጣ ታትሞ ከወጣበት ቀን ጀምሮ በስራ ላይ እንዲውል በሙሉ ድምጽ ወስኗል፡፡


Comments

ምንም አልተገኘም.

አስተያየቶችዎን ይተዉት.