በመዲናዋ ከ500 ሺህ በላይ በጎ ፈቃደኞች የሚሳተፉበት የበጋ በጎ ፈቃድ መርሀ ግብር ይፋ ተደረገ።
በአዲስ አበባ ከ500 ሺህ በላይ በጎ ፈቃደኞች የሚሳ ተፉበትና ከ911 ሺህ በላይ ዜጎች ተጠቃሚ የሚሆኑበት የበጋ በጎ ፈቃድ መርሀ ግብር ይፋ ተደርጓል።
የከንቲባ አማካሪ አቶ ጥላሁን ሮባ በማስጀመሪያ መርሀ ግብር ላይ ተገኝተው ባስተላለፉት መልዕክት በከተማችን አዲስ አበባ በጎ ፈቃደኝነት በሰላም፣ በልማትና በሰው ተኮር ተግባራት እያደረገ ያለው አዎንታዊ አስተዋፅዖ ከፍተኛ መሆኑን ተናግረዋል።
የበጎ ፈቃድ አገልግሎት እንደከተማ የራስን ችግር በራስ አቅም ለመፍታት የያዝነው የሰው ተኮር እቅዳችን አካል መሆኑን ነው አቶ ጥላሁን የተናገሩት። ከተማ አስተዳደሩ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት ሰው ተኮር የበጎ ፈቃድ አገልግሎቶችን አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ኃላፊው ጨምረው ገልፀዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የኅብረተሰብ ተሳትፎና በጎ ፈቃድ ማስተባበሪያ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ወ/ሮ አስራ ንጉሴ ባለፉት የለውጥ ዓመታት ከ42.5 ቢሊዮን ብር በላይ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት መሰጠቱን ገልፀዋል።
በጎነት የልብ ለልብ ግንኙነትን በማጠናከር ለሀገር ሰላምና እድገት የሚጫወተው ሚና ከፍተኛ ነው ያሉት ምክትል ኮሚሽነሯ በከተማችን ወጣቱንና መላ ነዋሪውን እያሳተፍን በተገበርነው የበጎነት ሰው ተኮር አገልግሎት ከኮቪድ ፈተና ጀምሮ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ተግዳሮቶችን እየተሻገርን የበርካታ ነዋሪዎችን ህይወት ቀይረናል ሲሉ አፅንዖት ሰጥተዋል፡፡
ባለፈው ክረምት በተካሄደው የበጎ ፈቃድ መርሀ ግብር በድግግሞሽ 2.4 ሚሊዮን በጎ ፈቃደኞች መሳተፋቸውን ያወሱት ወ/ሮ አስራት ንጉሴ 8.2 ቢሊዮን ብር የሚገመትና 1 ሚሊዮን 25 ሺህ 260 ዜጎችን ተጠቃሚ ያደረገ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ተሰጥቷል።
የ2018 ዓ.ም የበጋ በጎ ፈቃድ አገልግሎት "በጎ ፈቃደኝነት ለማኅበረሰብ ለውጥ!" በሚል መሪ ሀሳብ 500 ሺህ በጎ ፈቃደኞች የሚሳተፉበት መሆኑን የተናገሩት ወ/ሮ አስራት 12 ዋና ዋና እና 13 ንዑሳን መርሃ ግብሮች ተካተውበታል።
የከተማችንን ልማትና እድገት ለማፋጠንና የህብረተሰቡን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ለመቅረፍ በሚደረገው ጥረት ውስጥ በጎ ፈቃደኝነት ድርሻውን እንዲወጣ በማድረግ 911 ሺህ 200 የኅብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ለማድረግ 9.5 ቢሊየን ብር የበጋ በጎ ፈቃድ አገልግሎት ይሰጣል ብለዋል ኃላፊዋ፡፡
ሁሉም ባለድርሻ አካላት የበጋውን የበጎ ፈቃድ ፕሮግራም ውጤታማ እንዲሆን እንዲሁም በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ የሚገኙ ዜጎችን ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በትብብር እንዲሰሩ ጠይቀዋል።
ዘገባው:-የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የኅብረተሰብ ተሳትፎና በጎ ፈቃድ ማስተባበሪያ ኮሚሽን ነው
Comments
ምንም አልተገኘም.
አስተያየቶችዎን ይተዉት.