በልማት ኮሪደሩ የሚደረገው ርብርብ በአንድ በኩል...

image description
- ውስጥ Current Affairs    0

በልማት ኮሪደሩ የሚደረገው ርብርብ በአንድ በኩል የዜጎችን ህይወት ለማሻሻል በሌላ በኩል ደግሞ የከተማችንን ዕድገት ለማፋጠን ነው:: አቶ ሞገስ ባልቻ

በብልፅግና ፓርቲ የአዲስ አበባ ቅ /ፅ /ቤት ሀላፊ አቶ ሞገስ ባልቻ ለከተማችን ዕድገት ተገቢው ካሳ እና ምትክ ቤት ተሰጥቶአቸው ከመሀል ከተማ ወደ ለሚኩራ ክ/ከተማ ወረዳ 2 ፣ 6 እና 9 የጋራ መኖሪያ ቤቶች የተዘዋወሩ ዜጎች ያሉበትን ሁኔታ በመጎብኘት ማዕድ አጋርተዋል።

በብልፅግና ፓርቲ የአዲስ አበባ ቅ /ፅ /ቤት ሀላፊ አቶ ሞገስ ባልቻ በጉብኝታቸው ላይ እንደተናገሩት የልማት ተነሽዎች ለከተማችን ፣ ዕድገት፣ መሻሻል እና ብልፅግና ላደረጉት አስተዋፅዖ አዲስ አበባ እንደምታመሰግናቸው ገልፀው ህይወታቸው እንዲሻሻልም የአስተዳደሩ የቅርብ ክትትል እንደማይለያቸው አረጋግጠውላቸዋል።

በልማት ምክንያት ከመሀል ከተማ ለተነሱ ዜጎች ይኖሩበት ከነበረ የተሻለ ቤት ከመስጠት ባሻገር መሰል ጉብኝቶች የጎደሉ መሰረተ ልማቶችን በተቀናጀ መልኩ በፍጥነት ለማሟላት እንደሚያግዙ ጠቁመዋል።

ቤት ለቤት በመሄድ ጭምር በተደረገው ምልከታም ነዋሪዎች የተሻለ ቤት በማግኘታቸው ቢደሰቱም ያልተሟሉ መሰረተ ልማቶች ቶሎ እንዲሟሉ በጋራ ለመረባረብ ተጨማሪ ግብአት የሚሆን ሀሳብ መስጠታቸውን ሀላፊው አስረድተዋል።

የኮሪደር ልማቱ የከተማችንን ገፅታ የሚያሻሻል ትልቅ ፕሮጀክት በመሆኑ ክብርት ከንቲባ አዳነች አቤቤን ጨምሮ በየደረጃው በሚገኘው አመራር እና ባለሙያ 7 / 24 እየተሰራ መሆኑን ያስረዱት አቶ ሞገስ የሚደረገው ርብርብ በአንድ በኩል የዜጎችን ህይወት ለማሻሻል በሌላ በኩል ደግሞ የከተማችንን ዕድገት ለማፋጠን ነው ብለዋል።

የከተማ አስተዳደሩ ከመሀልም ከዳርም የሚገኙ ዜጎች ህይወት እንዲሻሻል እንደሚተጋ የገለፁት ሀላፊው ወደ ለሚ ኩራ ወረዳ 2 ፣ 6 እና 9 የጋራ መኖሪያ ቤቶች የመጡ ዜጎችን ህይወት ይበልጥ ለማሻሻል በዛሬው ዕለት በተደረገው ጉበኝት የተሳተፉ የክ/ከተማው እና የቤቶች ልማት አሰተዳደር አመራርና ባለሙያዎች ከሌሎችም ባለድረሻ አካላት ጋር በቅንጅት እንደሚሰሩ አስገንዝበዋል።

የልማት ተነሽዎችም እንዳረጋገጡት ቤቶቹ ፍትሀዊ በሆነ መንገድ በእጣ እንደተሰጧቸው ያወሱት አቶ ሞገስ የተማሪዎች ምገባን ጨምሮ ሌሎችንም አገልግሎቶች በሄዱባቸው አካባቢዎችም እንደሚያገኙአቸው አስረድተዋል።

ያልተሟሉ ነገሮች ካሉ በፍጥነት የሚሰራ ግብረሀይልም ወደ ተግባር መግባቱን የጠቆሙት ሀላፊው በየደረጃው በሚገኙ የአስዳደሩ መዋቅሮች ቅሬታዎችን ተቀብሎ ማስተናገድ የሚያስችል አሰራር መዘርጋቱንም ገልፀዋል።

የለሚ ኩራ ክ/ከተማ አሰተዳደር ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ታረቀኝ ገመቹ በበኩላቸው ለከተማችን ዕድገት ከመሀል ከተማ ተነስተው ወደ ክ/ከተማው የመጡ ነዋሪዎችን ህይወት ለማሻሻል በየቀኑ ክትትል እየተደረገ መሆኑን ጠቅሰው የተደረገው ጉብኝት እና ማዕድ ማጋራትም ዓለማው ተመሳሳይ መሆኑን አስገንዝበዋል።

በፊት ከነበሩበት የተሻለ ጥራት እና ስፋት ያለው ቤት ማግኘታቸውን " ከፈራረሰ ቀበሌ ቤት ተነስተን የፎቅ ቤት ባለቤት ሆነናል" በማለት አስተያየታቸውን የሰጡት የልማት ተነሽዎች ወደ አዲሱ ቤታቸው የገቡት በፍትሀዊ መንገድ በእጣ ቢሆንም ፎቅ ላይ የደረሳቸው አቅመ ደካሞች በልዩ መንገድ እንዲታይላቸው ፣ የመንገድ መሰረተ ልማቶች እንዲሟሉ ፣ የመብራት መቆራረጥ ዘላቂ መፍትሄ እንዲሰጠው ፣ያልተሟሉ የፍሳሽ መስመሮችም በፍጥነት እንዲሟሉ ጠይቀዋል።

ጉድለቶችን በፍጥነት ለማሟላት በየደረጃው ያለው አመራር የሚያደርገውን የተቀናጀ ርብርብ እና የቅርብ ክትትልም የልማት ተነሽዎች አድንቀዋል።


Comments

ምንም አልተገኘም.

አስተያየቶችዎን ይተዉት.