ከልማት ተነሺዎች ጋር በተያያዘ በከተማ ደረጃ እስካሁን 249 የሚደርሱ ቅሬታዎች ቀርበው ምላሽ አግኝተዋል፡- አቶ ሞገስ ባልቻ
በአዲስ አበባ ከተማ እየተካሄደ ባለው የኮሪደር ልማት ከልማት ተነሺዎች ጋር በተያያዘ በከተማ ደረጃ እስካሁን 249 የሚደርሱ ቅሬታዎች ቀርበው ምላሽ ማግኘታቸውን የአዲስ አበባ ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሞገስ ባልቻ ተናገሩ።
በኮሪደር ልማቱ አጠቃላይ የስራ ሂደት ላይ መግለጫ የሰጡት ኃላፊው በኮሪደር ልማት ስራው ለ4ሺ 360 ነዋሪዎች ቋሚ እና ግዜያዊ የስራ እድል መፈጠሩን ተናግረዋል።
የከተማ አስተዳደሩ እንደ ኑሮ ውድነት ያሉ የከተማዋን ነዋሪ አንገብጋቢ ችግሮች ለመፍታት በርካታ ተግባራትን ትኩረት ሰጥቶ እያከናወነ መሆኑን የተናገሩት አቶ ሞገስ አዲስ አበባ ከተማ የአፍሪካ መዲና እንዲሁም የአለም የዲፕሎማቲክ ማዕከል እንደመሆኗ ለኑሮ ምቹ የማድረግ እና ደረጃዋን የማሳደግ ስራ መስራት ስለሚገባ የኮሪደር ልማት ስራው እየተካሄደ መሆኑን ገልጸዋል።
በከተማዋ በተመረጡ አምስት ኮሪደሮች እየተካሄደ ያለው የኮሪደር ልማት በእቅድ ተይዞ እና ለአንድ አመት ገደማ ተጠንቶ ወደ ስራ መገባቱን የተናገሩት አቶ ሞገስ ባልቻ ከሀገራዊ ለውጡ በኋላ ሊሰሩ እና በተግባር ሊፈጸሙ የሚችሉ ፕሮጀክቶች ብቻ የሚጀመሩ በመሆናቸው የኮሪደር ልማቱም በመልካም የአፈጻጸም ሂደት ላይ ይገኛል ብለዋል።
ከኮሪደር ልማቱ ጋር ተያይዞ ለልማት ተነሺዎች ልዩ ትኩረት መሰጠቱን እና እንደየ ምርጫቸው የጋራ መኖሪያ ቤት፣ ከቀድሞ የተሻሉ የቀበሌ ቤት መኖሪያ ህንጻዎች፣ እንዲሁሞ ለግል ባለይዞታዎች ምትክ ቦታ እና ካሳ በመስጠት መስተናገዳቸውን ጠቁመው አዲስ በገቡባቸው አካባቢዎች ከመሰረተ ልማት ፣ ትምህርት ቤት ፣ጤና አገልግሎትን እና የመሳሰሉ ተቋማት መሟላታቸው ተገቢው ክትትል እየተደረገ እና ክፍተት ሲኖርም እየተሞላ መሆኑን ገልጸዋል።
ከልማት ተነሺዎች ጋር በተያያዘ በየደረጃው በተደራጀው የቅሬታ ማቅረቢያ ስርዓት 249 የሚደርሱ ቅሬታዎች መቅረባቸውን የተናገሩት አቶ ሞገስ አብዛኛዎቹ በእጣ ከደረሳቸው ቤት ቅያሬ ጋር የተያያዘ መሆኑን እና 83 ያህሉ ተገቢነታቸው ታይቶ መፈታታቸውን ተናግረዋል።
176 የሚሆኑት ቅሬታዎች ተገቢባ ለመሆናቸው ከአቅራቢዎቹ ጋር በግልጽ በመነጋገር ከመግባባት ላይ ተደርሷልም ነው የሉት።
የከተማ አስተዳደሩ በአሁኑ ወቅት ትኩረት ሰጥቶ የሚሰራው የተጀመሩትን አምስት የኮሪደር ልማቶች ለማጠናቀቅ ነው ያሉት ኃላፊው በሌሎች አካባቢዎች ተጨማሪ አዳዲስ ልማቶች ሊጀመሩ ነው በሚል የሚሰራጩ መረጃዎችም የተሳሳቱ መሆናቸውን ተናግረዋል።
Comments
ምንም አልተገኘም.
አስተያየቶችዎን ይተዉት.