የሳምንቱ መጀመሪያ ሰኞ ለእኛ ፍካትና ተስፋ የሚሰጠን ቀን ነው!
ሳምንታችንን አጨልመን አንጀምርም!
ከንቲባ አዳነች አቤቤ
‘ወርቃማ ሰኞ’ የሚል መጠሪያ የተሰጠውና በሳምንቱ መጀመሪያ ቀን ዘወትር ማለዳ የሚካሄደው የመማማሪያ መርሃ-ግብር ሁለተኛ ዓመት ዛሬ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ በተገኙበት ተከብሯል። ይህ ከሁለት ዓመት በፊት በክብርት ከንቲባ ሃሳብ አመንጭነትና መሪነት የተጀመረው መርሃ-ግብር ‘ጥቁር ሰኞ’ን ወደ ‘ወርቃማ ሰኞ’ የቀየረ ሆኗል። የከንቲባ ጽ/ቤት፣ የሰላምና ጸጥታ ቢሮ፣ የሥራ አስኪያጅ ጽ/ቤትና የኮሙኒኬሽን ቢሮ አመራሮችና ሰራተኞች የሚሳተፉበት ‘ወርቃማ ሰኞ’ ሦስት ግቦችን (ከተማችንን የብልጽግና ተምሳሌት እናደርጋለን፣ ስንተባበር ለውጥ እናመጣለን እና እዚህ ያለነው ለማገልገል ነው) በማነገብ የተጀመረ ነው።
በሁለተኛ ዓመት ክብረ በዓል አከባበር ላይ ተገኝተው መልዕክት ያስተላለፉት ከንቲባ አዳነች አቤቤ የሳምንቱን መጀመሪያ ሰኞን በፍካትና በተስፋ እንጂ አጨልመን አንጀምረውም ብለዋል። ይህ ለራስ እድገት አስፈላጊ የሆነው መርሃ-ግብር በአሁኑ ሰዓት ወደ ሁሉም የከተማዋ መዋቅሮች እንደተስፋፋ እና እየተተገበረ እንደሚገኝም ገልጸዋል።
በዕለቱ ከክብርት ከንቲባ መልዕክት ባሻገር ‘ወርቃማ ሰኞ’ በሚል ርዕስ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቲያትርና ባህል አዳራሽ ተውኔት ያቀረበ ሲሆን የሁለተኛ ዓመት የመርሀ-ግብሩ ጉዞም ለታዳሚው በገለጻ መልክ ቀርቧል።
Comments
ምንም አልተገኘም.
አስተያየቶችዎን ይተዉት.