መንግሥታችን ሕዝብን ያዳምጣል፣ ከሕዝብ ለሚነሱ ጥያቄዎች ተገቢ ምላሽ ይሰጣል። ዛሬ ከማለዳ አንስቶ ከነዋሪዎቻችን ጋር ሰፊ ውይይቶችን አካሂደናል።
ውይይቶቹ በመዲናችን አዲስ አበባ በሚገኙ በሁሉም ክፍለ-ከተሞች በስፋት ተካሂደዋል።
የሃይማኖት አባቶች፣ የአገር ሽማግሌዎች፣ ወጣቶችና ሴቶች፣ የንግዱ ማህበረሰብ፣ ባለሀብቶችና ምሁራንን ጨምሮ የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ተወካዮች ተሳታፊ ሆነዋል።
የጉባ ብስራቶች የመደመር መንግስት ቱሩፋት በሚል ርዕስ ከዚህ ቀደም በተለያዩ የሕዝብ መድረኮች ላይ ከነዋሪዎቻችን ለተነሱ ጥያቄዎች፣ ቅሬታዎች እና አስተያየቶች በተግባር የተሰጡ ምላሾች፣ እንዲሁም ቀሪ ሥራዎችን አስመልክቶ በዝርዝር ቀርበው ውይይት ተካሂዶባቸዋል።
የከተማ አስተዳደራችን ከፍተኛ አመራሮችና ሚኒስትሮች መድረኮቹን በመምራት ከህዝብ የተነሱ ጥያቄዎች ላይ ማብራሪያ ሰጥተዋል፤ የቤት ስራም ወስደዋል።
ባለፉት የለውጥ ዓመታት በከተማችን በተለያዩ የልማት ሥራዎች አስደናቂ ስኬቶች የተመዘገቡት መንግሥትና ሕዝብ አንድ ሆነው በመቀናጀትና በመናበብ ሊፈጽሟቸው በመቻላቸው ነው።
ዛሬም በመንግሥትና በሕዝብ ትብብር የተሰሩ በርካታ ሥራዎችን እና የተመዘገቡ ውጤቶችን ይበልጥ ለማጠናከር፣ እንዲሁም የሕዝብን ተሳትፎ ይበልጥ በሚያረጋግጡ ቀጣይ የጋራ ዕቅዶች ላይ እንደ ወትሮው ከነዋሪዎቻችን ጠቃሚ ግብዓት ያገኘንበት ፍሬያማ የውይይት መድረክ ነበር።
ውድ ነዋሪዎቻችን፣ ለሰጣችሁን ገንቢ አስተያየት፣ ለነበራችሁ ከፍተኛ ተሳትፎ፣ ለሰጣችሁን ውድ ጊዜ በራሴና በከተማ አስተዳደሩ ስም ከልብ አመሰግናለሁ።
በቀጣይም ይበልጥ ተቀራርበን መሥራታችንን እንቀጥላለን።
ፈጣሪ ኢትዮጵያን እና ሕዝቦቿን ይባርክ!
ከንቲባ አዳነች አቤቤ
Comments
ምንም አልተገኘም.
አስተያየቶችዎን ይተዉት.