መጪው የ2018 ዓ.ም የከተራና የጥምቀት በዓላት በሰላም ተከብሮ እንዲውል ሁሉም የበኩሉን አስተዋጽኦ እንዲወጣ ጥሪ ቀረበ።
በአዲስ አበባ ከተማ ብሎም በአጎራባች በሸገር ከተሞች መጭው የከተራና የጥምቀት በዓል ሀይማኖታዊ ትውፊቱን ጠብቆ እንዲከበር ለማድረግ የአዲስ አበባ ከተማ ሰላምና ጸጥታ አስተዳደር ቢሮ የጸጥታ ስራዎችን በማጠናቀቅ ላይ የሚገኝ ሲሆን በዛሬው ዕለትም የአዲስ አበባ ከተማ ሰላምና ጸጥታ አስተዳደር ቢሮ፣ከአዲስ አበባ ፖሊስ ኮምሽን፣ከአዲስ አበባ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ እና በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ጋር በመተባበር የከተራ እና የጥምቀት በዓል አከባበርን በማስመልከት የማጠቃለያ ውይይት ተደርጓል።
መጋቢ ታምራት አበጋዝ የአዲስ አበባ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ዋና ጸሀፊ የዛሬው የማጠቃለያ መድረክ ዋና ዓላማ በዓሉን አስመልክቶ በየወረዳ ውይይት ሲደረግ የቆየ እንደሆነ አንስተው፣ የጥምቀት በዓል ሃይማኖታዊ ዕሴቱን ጠብቆ በሰላም እንዲከበር የጋራ ተግባቦት ለመፈጠር እና የበዓሉ ድምቀት ያደበዝዛሉ ወይንም ስጋት ሊሆኑ ይችላሉ የሚባሉ ታሳቢ ችግሮች ካሉ የጋራ ግንዛቤ በመፍጠር የተዘጋጀ መድረክ እንደሆነ ገልፀዋል።
በዓሉ ከመንፈሳዊነትቱ በተጨማሪ ለከተማችንም ሆነ ለሀገራችን በርካታ ማህበራዊ፣ባህላዊ እና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳዎች አካቶ የያዘ በዓል ሲሆን በዓሉ በዋናነት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ቢሆንም አለም በቅርስነት መዝግቦ የያዘው የሁሉም ኢትዮጵያዊ እንዲሁም የዓለም ህዝብ በጉጉት የሚጠብቀው በዓል እንደሆነም ገልዋል።
ይህ በዓል ከመንፈሳዊነቱ ባሻገር ሀገራዊ መግባባትን እና አንድነትን በማጎልበት በማህበረሳባችን ውስጥ ሰላምን መተሳሰብንና መግባባትን በመፍጠር የሰላም የፍቅርና የይቅርታ መንፈስ የሚያጠናክር በብዙኃነት ውስጥ አንድነትን አጉልቶ የሚያሳይ የተለያዩ የብሔሮችና ባህሎች ውስጥ አማኞቹ በአንድ ላይ መሳተፋቸው የጋራ ባህልን የሚያጠናክር እንዲሁም ዓለም አቀፍ የባህል ትኩረትን የሚስብና ኢትዮጲያ በዓለም ፊት እንድትታወቅ የሚያደርግ በዓል መሆኑን አንስተዋል።
ብጹ አቡነ ሕርያቆስ የአዲስ አበባ፣ የሐዲያ የስልጤ አህጉር ስብከት ሊቀጳጳስ እና የአዲስ አበባ የሀይማኖት ተቋማት ጉባኤ የቦርድ ሰብሳቢ በመድረኩ በመገኘት እንደተናገሩት መድረኩ ታላቁ የጥምቀት በዓል በምን ዓይነት መልኩ ማክበር እንዳለብን ለመወያየት የተዘጋጀ እንደሆነ አንስተው፣ በዓሉን ለማክበር ከውጭ ሀገር እንግዶች እየገቡ እንደሆነ በመግለጽ፣የሃይማኖት አባቶች በየቤተ እምነቱ ሆነ በተገኘው አጋጣሚ ሰላምን በማወጅ ስለአንድነት፣ፍቅርና እርቅ በመስበክ ህዝቡ በዓሉን በሰላም እንዲያከብር የበኩሉን ሚና መወጣት እንዳለበት አሳስበዋል።
በውይይቱ ላይ በክብር እንግድነት የተገኙትን ወ/ሮ ሊዲያ ግርማ የአዲስ አበባ ከተማ ሰላምና ጸጥታ አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ ባስተላለፉት መልዕክት ኢትዮጵያ ሀገራችን የብዙ ማንነቶች ባለቤትና በብዝሀነት ተቻችለውና ተከባብረው በሰላም የሚኖሩባት ተምሳሌት እንደመሆኗ መጠን ሁሉም እንደየ እምነቱ በአስተምህሮዎቻቸው ስለ ፍቅር እንድነት በማስተማር ሀላፊነትን ይወስዳሉ በማለት የአደባባይ በዓላት በሚከበርበት ወቅት በርካታ እንቅስቃሴዎች በከተማው ላይ የሚደረግበት መጭው የከተራና የጥምቀት በዓልም በዓለም ቅርስነት የተመዘገበ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ባለፉት ወራት ያከበርናቸው ሀይማኖታዊ የአደባባይ በዓላት በሰላም ተከብረው ማለፋቸው ነዋሪው ቀናነትን ያሳየበት እንደነበር ጠቅሰዋል
ሀላፊዋ አያይዘውም በቀጣይ ሳምንታትም የሚከበሩት የከተራና ጥምቀት በዓላት መላው የከተማችን ነዋሪ በህብረት ወቶ የሚያከብረው በዓል እንደ መሆኑ ሀይማኖታዊ ክብረ በዓል የመቻቻልና የመከባበር ኢትዮጵያዊ እሴቶቻችን በጠበቀና ወንድማማችነትና እህትማማችነት በሚያዳብር እንዲሁም የሀገርን ገጽታ በዓለም አቀፍ ደረጃ በሚገባ መልኩ ያለምንም የጸጥታ ችግር ፍጹም ሰላማዊ በሆነ መልኩ እንዲከበር ለማስቻል ከጸጥታው ተቋማት ጋር በመቀናጀት ክብረ በዓሉ የፖለቲካ ፍላጎት ማስፈጸሚያ ለማድረግና የጸጥታ ችግር ለመፍጠር የሚሞክሩ አካላትን በመከላከል የሀይማኖት አባቶች እና የሀይማኖት አደረጃጀቶች እንዲሁም አጠቃላይ የበዓሉ አስተባባሪዎችና መላው የከተማው ነዋሪ በዓሉ በሰላም ተከብሮ እንዲውል ሀላፊነታቸውን እንዲወጡ መልዕክት አስተላልፈዋል።
በመጨረሻም ኮምሽነር ጌቱ አርጋው የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮምሽን ጠቅላይ መምሪያ ዋና አዛዥ ሀሳባቸውን ሲገልጹ በዓሉ መንፈሳዊ ይዘት ያላቸውን መልዕክቶችን በማስተላለፍ ብቻ ማህበረሰቡ ሀላፊነቱን እንዲወጣ በመጠቆም ከበፊቱ በበለጠ መልኩ በዓሉ በሰላም ተከብሮ እንዲውል ለማስቻል ከተማውንና ሀገርን የሚመጥን የጸጥታ አጠባበቅ በመስራት ደረጃ ስራዎች ተሰርተው መጠናቀቃቸውን ገልጸዋል።
በዓሉ በሰላምና ሀይማኖታዊ እሴቱን ጠብቆ እንዲከበር ከማን ምን ይጠበቃል የሚል መነሻ ጽሁፍ ያቀረቡት ክቡር ዶክተር ቆሞስ አባ ቃለጽድቅ አካለ ወልድ ሙሉጌታ ሲሆኑ በኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት የሰበካ ጉባዔ ማደራጃ መምሪያ ሀላፊ ሲሆኑ ጽሁፉን መነሻ በማድረግም ሰፊ ውይይት ከተደረገ በሏላ ቀጣይ በበዓሉ አከባበር ላይ አቅጣጫ ተሰጥቶ መድረኩ ተጠናቋል።
Comments
ምንም አልተገኘም.
አስተያየቶችዎን ይተዉት.