መጪው የከተራና የጥምቀት በዓል በሠላም እንዲከበር አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት አጠናቆ ወደ ስራ መግባቱን ጥምር የፀጥታና የደህንነት ግብረ ኃይል አስታወቀ።
በክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ በድምቀት የሚከበረውን የከተራና የጥምቀት በዓል በሠላም እንዲከበር መላው የፀጥታ አካላት ዝግጅታቸውን አጠናቀው ወደ ስራ መግባታቸውን ጥምር የፀጥታና ደህንነት ግብረ ኃይል አስታውቆ በዓሉን አስመልክቶም የጸጥታ ዕድቅ ቀርቦ ስምሪት ተሠጥቷል።
የፌዴራል ፖሊስ ወንጀል መከላከል ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ም/ኮሚሽነር ጄነራል መላኩ ፋንታ፣ የአዲስ አበባ ከተማ ሠላምና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ሊዲያ ግርማ፣ የአዲስ አበባ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ኮሚሽነር ጌቱ አርጋው፣ የፌዴራል የአዲስ አበባ እና የሸገር ከተማ አስተዳደር ፖሊስ መምሪያ፣ ከብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት እና ሌሎች ከፍተኛ አመራሮች በተገኙበት ውይይት ተደርጓል፡፡
የፌደራል ፖሊስ የወንጀል መከላከል ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ም/ኮሚሽነር ጄነራል መላኩ ፋንታ ባስተላለፉት መልእክት በከተማዋ የሚከወኑ በርካታ በዓላት በሰላም እንዲጠናቀቁ መላዉ የፀጥታ ኃይል ጠንካራ የካበተ ልምድ እንዳለዉ አስታውሰዉ በቅርቡ የተደረገዉ የአእላፋት ዝማሬ ስነ ስርዓት አንዱ መሆኑን ገልፀዉ ፍጹም ሠላማዊ በሆነ መንገድ መጠናቀቁ ጥምር የጸጥታና ደህንነት የጋራ ግብረ ኃይሉ ከመላው የከተማችን ነዋሪዎችና ልዩ ልዩ አደረጃጀቶች ጋር በጋራ በመስራቱ የመጣ ውጤት መሆኑን ተናግረዋል፤ በተመሳሳየይ የጥምቀትና የከተራ በዓል ፍጹም ሠላማዊ እንዲሆን ሁሉም አመራርና አባላት ኃላፊነቱን በብቃት እንዲወጣ የስራ መመሪያ ሰጥተዋል ።
ሌላው በበዓሉ ላይ በዜጎች ላይ ግጭት የሚፈጥሩ ኃይማኖታዊ ያልሆኑ መልዕክቶች በዓሉን የማይመጥኑና በህግ የተከለከሉ ነገሮችን በዓሉ ወደሚከበርባቸዉ ቦታዎች ይዞ መምጣት የተከለከለ መሆኑን ም/ኮሚሽነር ጄነራሉ ገልጸዋል።
የአዲስ አበባ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ኮሚሽነር ጌቱ አርጋው በበኩላቸው ለጋራ ደህንነት ሲባል የፀጥታ ሐይሉ ለሚያከናዉነው የፀጥታ ስራ ህብረተሰቡ ተባባሪነቱን አጠናክሮ እንዲቀጥል አሳስበው በከተማችን በሚገኙ በ66ቱም የታቦታት ማደሪያ ቦታዎች ላይ ከሠላም ወዳዱ የከተማችን ነዋሪዎችና ከጸጥታ መዋቅሩ ጋር ጠንካራ የሠላምና ደህንነት ስራ ይሠራልም ብለዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሠላምና ጸጥታ አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ሊዲያ ግርማ በበኩላቸው በከተማዋ ከሚገኙ አብያተ ክርስቲያናት አባቶችና አመራሮች፣ ከህብረተሰቡ፣ ከሠላም ሠራዊትና ከልዩ ልዩ አደረጃጀቶች ጋር ቀደም ብሎ ውይይት መደረጉን ተናግረው ህብረተሰቡም ለበዓሉ ሠላማዊነት ተገቢውን ትብብር እንዲያደርግ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
በስብሰባው ላይ የተገኙ አመራሮች በዓሉ በሠላም ተከብሮ እንዲያልፍ ያደረጉትን ቅድመ ዝግጅት አቅርበውም ሠፊ ውይይት ተደርጎበታል። መጪው የከተራና የጥምቀት በዓል የሠላምና የደስታ እንዲሆን መልካም ምኞቱን የገለጸው የፀጥታና ደህንነት የጋራ ግብረ ኃይል ህብረተሰቡ ለፀጥታ ስጋት የሆኑ አጠራጣሪ ነገሮች ሲያጋጥሙት በነጻ የስልክ መስመሮች 990፣ 991፣ 987፣ 816 እንዲሁም በ011-1-26-43-59፣ 011-5-52-63-02/03፣ 011-5-52-40-77፣ 011-5-54-36-78 እና 011-5-54-36-81 እንዲሁም በእጅ ስልኮች የዜጎች ተሳትፎ መተግበሪያን (Citizen Engagement Application) EFPApp በመጠቀም ጥቆማ በመስጠትና አስፈላጊውን ትብብር በማድረግ የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣም ጥሪውን ያስተላልፋል፡፡
Comments
ምንም አልተገኘም.
አስተያየቶችዎን ይተዉት.