" በስራ ፈላጊዎቻችን ልክ በቂ ፀጋዎችም እንዳሉን ለይተን ወደ ስራ በመግባታችን አሰራራችንን በመፈተሽ ቃልአችንን በተግባር መተርጎም ይገባናል - አቶ ሞገስ ባልቻ
የከተማ እና የክ/ከተማ ከፍተኛ የስራ ሀላፊዎች በአገር ደረጃ በስራ ዕድል ፈጠራ እና የኑሮ ውድነቱን ለማረጋጋት የተቀመጠው አቅጣጫ በከተማችን ያለውን አተገባበር ገምግመዋል።
በብልፅግና ፓርቲ የአዲስ አባባ ቅ /ፅ /ቤት ሀላፊ አቶ ሞገስ ባልቻ በግምገማው ላይ እንደተናገሩት አገራዊ ዕቅድ ወጥቶለት የተቀናጀ ጥረት እየተደረገ የሚገኘው የስራ ዕድል ፈጠራ እና የኑሮ ውድነትን የማረጋጋት ጉዳይ በከተማችንም በጠንካራ ሱፐርቪዥን የታገዘ ርብርብ እየተደረገ እንደሚገኝ አስረድተዋል።
የህዝባችን የኑሮ ጫና ለማቃለል በተከናወነው ስራ በተወሰነ መልኩም ቢሆን በአንዳንድ ምርቶች ላይ የገበያ መረጋጋት መፈጠሩን የጠቀሱት አቶ ሞገስ መሰረታዊ የሆነ ለውጥ ለማስመዝገብ ምርትና ምርታማነትን ከማሳደግ ባለፈ ህገ -ወጥ የንግድ ሰንሰለቶችን ስርዓት የማስያዙ ተግባርም ህዝባችንን በማስተባበር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልፀዋል።
የስራ ዕድል ፈጠራው ስኬቶች ቢኖሩትም አሁንም በልዩ ትኩረት ሊመራ እንደሚገባ ያመላከቱት አቶ ሞገስ በስራ ፈላጊዎቻችን ልክ በቂ ፀጋዎችም እንዳሉን ለይተን ወደ ስራ በመግባታችን አሰራራችንን በመፈተሽ ቃልአችንን በተግባር መተርጎም ይገባናል ብለዋል።
የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ አቶ ጃንጥራር አባይ የ90 ቀናት ዕቅድን ከመደበኛ ስራዎች ጋር አስተሳስሮ ለመምራት በተደረገው ጥረት የተሻሉ ስኬቶች መመዝገባቸውን ጠቅሰው የበጀት ዓመቱ እየተገባደደ ስለሆነ ጉድለቶችን ማረም ብቻ ሳይሆን ፈጥኖ ማረም እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
ከተማዋ እየተገበረችው ያለውን ግዙፍ ሰው ተኮር ፕሮግራም በሚመጥን መልኩ የከተማችንን የገቢ ምንጭ ማስፋት እንደሚገባም አቶ ጃንጥራር አስረድተዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የስራ ክህሎት ቢሮ ሀላፊ አቶ ጥራቱ በየነ የ90 ቀናት የንቅናቄ ዕቅድ የጋራ ተደርጎ ወደ ስራ ከተገባበት ጊዜ ጀምሮ አመራሩ ከሌሎች ስራዎች ጋር አስተሳስሮ እንዲመራ በማድረግ ህዝባችንን በማስተባበር የመልማት ፀጋዎቻችንን አሟጦ ለመጠቀም እንቅስቃሴ እየተደረገ መሆኑን ጠቅሰዋል።
በከተማችን እየተገነቡ የሚገኙ ግዙፍ ፕሮጀክቶች የስራ ዕድል እና ሌሎች ፀጋዎችን ይዘው መምጣታቸውን የጠቀሱት አቶ ጥራቱ በግንባታ ላይ ያሉት የልማት ኮሊደር፣ የጫካ ፕሮጀክት እና ፓርኮችም ብዙዎችን ተጠቃሚ እያደረጉ መሆኑን አስረድተዋል።
በውይይቱ ላይ የተሳተፉ የሴክተር ተቋማት እና የክ /ከተማ አመራሮች የህዝባችን የኑሮ ጫና ለማቃለል እና ወጣቶችንና ሴቶችን የስራ ዕድል ተጠቃሚ ለማድረግ እየተከናወኑ ያሉ ተግባራትን እንዲሁም በቀጣይ ቅንጅታዊ ርብርብ የሚጠይቁ ጉዳዮችን የጋራ አድርገዋል።
Comments
ምንም አልተገኘም.
አስተያየቶችዎን ይተዉት.