"የኮሪደር ልማቱ ከፍተኛ ልምድ የተገኘበት እና የሥራ ባህልን የቀየረ ነው"፡- አቶ ጃንጥራር ዓባይ
የኮሪደር ልማቱ ከፍተኛ ትምህርት እና ልምድ የተገኘበት እንዲሁም የሥራ ባህልን የቀየረ ነው ሲሉ ምክትል ከንቲባ ጃንጥራር ዓባይ ገለጹ።
የኮሪደር ልማቱን አስመልክቶ ከምክር ቤት አባላት ለተነሡ ጥያቄዎች ምላሽ የሰጡት ምክትል ከንቲባው፣ በኮሪደር ልማቱ ለከተማዋ ትልቅ ኢንቨስትመንትን የፈጠረ መሆኑን አውስተው ሥራውን በአጭር ጊዜ ለማጠናቀቅ ርብርብ እየተደረገ መሆኑንም ጠቅሰዋል።
ከዚህ በፊት ያልነበረ የመሠረተ ልማት ቅንጅት የታየበት እና የከተማዋን ደረጃ የሚያሳድግ መሆኑንም ገልጸዋል።
በልማት ሥራው ምክንያት ከአካባቢያቸው የሚነሡ ነዋሪዎችን አስመልክቶ የሚነሡ የተሳሳቱ አሉባልታዎች እንደነበሩ ጠቁመው፣ በኮሪደር ልማቱ የታየው አፈፃፀም አሉባልታዎቹ መሠረተ ቢስ መሆናቸውን ያሳየ እና በእርግጥም ሰው ተኮር ልማት የሚለውን አስተሳሰብ በትክክልም ያረጋገጠ ነው ሲሉም ተናግረዋል።
የልማት ሥራ መጀመሪያም ሲታሰብ ጀምሮ በጥናት የተደገፈ እና በየደረጃው ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ተከታታይ ውይይቶች የተካሄዱበት ነው ያሉት አቶ ጃንጥራር፣ በውይይቱ ወቅት በነዋሪው ለሚነሡ ጥያቄዎች እና ስጋቶች ምላሽ የሚሰጡ ሁኔታዎች ተመቻችተው ወደ ሥራ የተገባበት መሆኑንም አንሥተዋል።
ቅድሚያ ለልማት ተነሺዎች ቤት እና የመሥሪያ ቦታ የሚያገኙበት ሁኔታ የተመቻቸበት ሁኑታ መፈጠሩንም አስረድተዋል።
የግል ቤቶችንም በተመለከተ ማልማት ለሚችሉ ዕድል የተሰጠበት እና አቅም ለሌላቸው ደግሞ የመኖሪያ ቤት እና መሬት እንዲያገኙ የተደረገበት ሁኔታ መኖሩንም ገልጸዋል።
በልማት ሥራው ነዋሪዎችን በሚያስገድድ እና በሚያስቀይም ሁኔታ የተሠራበት ሁኔታ እንደሌለ ያወሱት አቶ ጃንጥራር፣ ችግር ሲኖር ችግሩ እየታየ፣ እየተገመገመ እና እየታረመ የሄደበት ሁኔታ መኖሩንም ጠቅሰዋል።
ከኤምባሲዎች ጋር በተያያዘ ሥራውን ለማስቀጠል በውይይት እና በመግባባት ለማስኬድ እየተሠራ እንዳለ ጠቁመው፣ በተለይም ጉዳዩ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እና በጠቅላይ ሚኒስትሩ በውይይት የሚፈታ መሆኑን አስረድተዋል።
እስካሁን ባለው ሂደት የኬኒያ ኤምባሲ በተወሰነ ደረጃ አጥር የማንሣት ሁኔታ እንዳለ እና ሌሎቹ ኤምባሲዎችም ከአገሮቻቸው ጋር መወያየት ስለሚፈልጉ በቀጣይ በውይይት ችግሩን ለመፍታት እየተሠራ መሆኑን አብራርተዋል።
Comments
ምንም አልተገኘም.
አስተያየቶችዎን ይተዉት.