ደረሰኝ የማይቆርጡ ነጋዴዎች ላይ የተቀናጀ እርምጃ ተወሰደ፦ 32 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ውለዋል
በመዲናዋ የንግድ ሥርዓቱን ፍትሐዊነት ለማረጋገጥ የአዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮ ከአዲስ አበባ ፖሊስ ጋር በመቀናጀት ባካሄዱት ድንገተኛ ኦፕሬሽን 32 ግለሰቦች እጅ ከፍንጅ ተይዘዋል።
ቅዳሜ ጥር 23 ቀን 2018 ዓ.ም መርካቶን ጨምሮ በተለያዩ አካባቢዎች በተደረገው በዚህ ክትትል፣ በ19 ሥጋ ቤቶች እና በ6 የግንባታ ዕቃዎች መሸጫ ድርጅቶች ላይ ህጋዊ እርምጃ ተወስዷል።
የመንግሥትን ግብር ለመሰወር ያለ ደረሰኝ ሽያጭ ሲያከናውኑ የተገኙ የንግድ ድርጅት ባለቤቶች እና ሠራተኞች በአሁኑ ወቅት በፖሊስ ቁጥጥር ስር ሆነው ምርመራ እየተካሄደባቸው ይገኛል።
ቢሮው ከዚህ ቀደም በጎማ፣ በኤሌክትሮኒክስና በኮንስትራክሽን ዘርፎች መሰል እርምጃዎችን መውሰዱ የሚታወስ ሲሆን፣ በቀጣይም በሌሎች ዘርፎች ኦፕሬሽኑ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቋል።
ማንኛውም የንግድ ግብይት በደረሰኝ ብቻ እንዲከናወን ያሳሰበው ቢሮው፣ ኅብረተሰቡ መሰል የሕግ ጥሰቶችን ሲመለከት በ7075 ነፃ የጥሪ መስመር እንዲያጋልጥ ጥሪ አቅርቧል።
የንግዱ ማህበረሰብ ከእንዲህ መሰል የወንጀል ድርጊቶች በመታቀብ የሕግ የበላይነትን እንዲያከብር በድጋሚ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷል።
Comments
ምንም አልተገኘም.
አስተያየቶችዎን ይተዉት.