#የጠሚሩምላሾች #PMOEthiopia

image description
- ውስጥ Current Affairs    0

#የጠሚሩምላሾች #PMOEthiopia

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከፓርላማ አባላት ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች የሰጡት ምላሽና ማብራሪያ ማጠቃለያ - ክፍል 2

የሰላም ጉዳይ

ኢትዮጵያ ውስጥ በሰላም እጦት እንድንኖር ካደረጉን እና ካልተላቀቅንባቸው ምክንያቶች መካከል አንደኛው ከጥንት የተጠባነው ልዩነቶችን በሃይል ብቻ የመፍታት ልምምድ ነው። ሁለተኛው ደግሞ አሁንም ከጥንት የመጣ የባንዳነት ልምምድ ሲሆን ሶስተኛው የጠላቶቻችን ኢትዮጵያ ካደገች የሚል ያልተቋረጠ ስጋት ነው።

ኢትዮጵያን የማጽናት ጉዞ

በኢኮኖሚ፣ በተቋማት ግንባታ የማድረግ አቅማችንን የምናሳድገው ኢትዮጵያን የሚያጸኑ ምሶሶዎችን መጠበቅ ግዴታ ስለሆነ ነው። ለአብነትም የኢትዮጵያ አየር ሃይል በለውጡ ማግስት አንድ ሄሌኮፕተር ብቻ የነበረ ሲሆን፤ አሁን ላይ የተለያዩ ስምና ተግባር ያለችው ከ100 በላይ አውሮፕላኖችን ታጥቋል። ይህ የተቋም ግንባታ ነው። አሁንም ቢሆን ሀገር ከመጠበቅ ጎን ለጎን የትኛውም የውስጥ ሃይል ወደ ሰለማዊ መንገድ ሲመለስ ለይቅርታ ዝግጁ መሆን አለብን ጉዳያችን ኢትዮጵያ ብቻ መሆን አለበት።

የወልቃይት አካባቢ የተፈናቃዮች ጉዳይ

የወልቃይት አከባቢ ነዋሪዎች በሰላማዊ መንገድ የመኖር መብት አላቸው። ይህን የፌደራል መንግስት በጽኑ የሚያምነው ጉዳይ ነው። ነገር ግን የአማራና የትግራይ ክልሎች በወልቃይት ጉዳይ ለረዥም ጊዜ የይገባኛል ጥያቄ ሲያነሱ ቆይተዋል። ሆኖም የፌደራል መንግስት እያለ ያለው ሰው አይፈናቀል ባለበት ይመለስ፤ ራሱን ያስተዳደር፤ ራሱ ጥያቄውን ይመልስ ነው። ማንም ከውጭ ሆኖ ሊወስንለት አይገባም።

የትግራይ ህዝብ በፖለቲካ አውድ ውስጥ ተዋንያን መሆን አለበት!

የትግራይ ህዝብ ሰላም፣ ልማት ይፈልጋል። የትግራይ ህዝብ አሁን ካለበት ችግር ወጥቶ ራሱ ተግቶ ሰርቶ መለወጥ የሚፈልግ ሰላም ወዳድ ህዝብ ነው። ከሌሎች ወንድም ኢትዮጵያዊያን ጋርም በጋራ መስራት ማደግ ይፈልጋል። ነገር ግን የትግራይ ህዝብ በፖለቲካ አውድ ውስጥ መድረክ እንጂ ተዋንያን መሆን አልቻለም። መድረክ ሌሎች እጫወቱበታል እንጂ ራሱ አይጫወትም። በመሆኑም የትግራይ ህዝብ በራሱ ተዋንያን መሆን አለበት። ለዚህ ደግሞ አዲስ የፖለቲካ አስተሳሰብ ያስፈልጋል። በትግራይ ያሉ ፖለቲከኞችም ከአጃቢ ተዋንያን ወደ መሪ ተዋንያን መሸጋገር አለባቸው።

የዘንድሮውን ምርጫ በሚመለከት

የዘንድሮው ምርጫ ሰላማዊ፣ፍትሃዊና አካታች እንዲሁም ካለፈው ምርጫ የተሻለ እንዲሆን መንግስት አበክሮ እየሰራ ነው። ምርጫውን በሚመለከት ለኢትዮጵያ ህዝብ ያለኝ መልስ በውጤት እንየው ነው። በእርግጠኝነት መናገር የምፈልገው ጉዳይ ይህ ፓርላማ በብዙ መልኩ በርካታ ድምጾች የሚሰሙበት ይሆናል። ምርጫው በሰላም ይከናወናል፤ በምርጫ የሚሳተፉ ሃይሎችም ተጠቃሚ ይሆናሉ።

አካታች ሀገራዊ ምክክርን በሚመለከት

ኢትዮጵያዊያን ለዘመናት ጦርነትን ሰርተዋል፤ የአሁኑ ትውልድ ደግሞ በውይይት ሀገርን መስራት፣ መገንባት አለበት። ከዚህ አኳያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ አጀንዳዎችን ለይቷል። የተሻለ ስራም ሲያከናውን ቆይቷል። በቀጣይም በርካቶችን ባካተተ መልኩ አጀንዳዎቹ ላይ ጥልቅ ውይይት በማድረግ ሃሳቦችን እንደሚያቀርብ ይጠበቃል። እስካሁን ባለው ሂደትም ኢትዮጵያዊያን የተቀራረበ ፍላጎት እንዳላቸው ትምህርት የሰጠ ነው።

የአፍሪካ ቀንድ ከባቢን በሚመለከት

የአፍሪካ ቀንድ እንዳይቀደድ የተሰፋ እንዳይጣመር የተቀየደ ከባቢ ነው። በባህልና ቀንቋ የሚተሳሰሩ ህዝቦች ያሉበት ቢሆንም ከፍተኛ ፉክክርና ጣልቃ ገብነት ያለው ከባቢ ነው። የሁለቱ ውሃዎች ጉዳይ እኛንም እያተረማመሰ በእኛ ጉዳይ የሚገቡ ሃይሎችን እያሰፈ አንዱ ለአንዱ መከታ ሊሆን ሲገባው ችግር አስተላላፊ ሆነ። በዚህ ምክንያት ቀጠናው የራሱ ችግር ያለበት በመሆኑ ይህን ለማስፋት ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ ነው። እንደሚሳካም እምነት አለኝ።

 


Comments

ምንም አልተገኘም.

አስተያየቶችዎን ይተዉት.