"ከተማዋ የአፍሪካ መዲና እና የዓለም የዲፕሎማሲ ማዕከልነቷን በሚያረጋግጥ መልኩ ዘርፈ ብዙ የልማት ስራዎች ተከናውነውባታል፡፡"አቶ ጃንጥራር አባይ
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አቶ ጃንጥራር አባይ በዳጉ ስርጭት ላይ ባደረጉት ቃለ ምልልስ ከተማዋ የአፍሪካ መዲና እና የዓለም የዲፕሎማሲ ማዕከልነቷን በሚያረጋግጥ መልኩ ዘርፈ ብዙ የልማት ስራዎች የተከናወኑባት ነች ሲሉ ገልፀዋል፡፡
ልማቱ ለሌሎች አፍሪካ ሃገራት ጭምር ምሳሌ ሊሆን የሚችል መሆኑን የጠቀሱት ምክትል ከንቲባዉ ይህም "ዘላቂ የዉሃ አቅርቦት፤ደህንነቱ የተጠበቀ የንፅህና አጠባበቅ ስርዓትን ማረጋገጥ" የሚለዉን የህብረቱ መሪ ቃል በተጨባጭ ማሳያ ነዉ ብለዋል፡፡
ከተማችን ለጉባዔው ስኬታማነት የኢንቨስትመንት መሰረተ ልማቶችን በማስፋት፣ የሆቴል አገልግሎቶችን በማዘመን እና የቱሪዝም መዳረሻዎችን በማስፋትና በማስዋብ እንግዶች ቆይታቸውን እንዲያራዝሙ የሚያስችሉ ምቹ ሁኔታዎች መፈጠሩን ተናግረዋል።
አያይዘዉም ቀደም ሲል የነበሩ የቆሸሹ ወንዞች እና ኋላቀር የፍሳሽ ማስወገጃ እና የደረቅ ቆሻሸ ዘዴዎች በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደ ዘመናዊነት ተቀይረው በዘላቂነት ለነዋሪዎችና ለእንግዶች ምቹ እንዲሆኑና ለአረንጓዴ የልማት ስራ እንዲዉሉም ተደርጓል ብለዋል፡፡
የአካባቢ ጥበቃን ከማጠናከር አኳያም ባለቤት ያለዉ የአሰራር ስርዓት በመዘርጋት እና ከቴክኖጂ ጋር በማቆራኘት ከልማቱ ጎን ለጎን ዘላቂነትን ታሳቢ ያደረገ ስራ እየተሰራ መሆኑ በማከል ጠቁመዋል፡፡
የተሳለጠ የትራፊክ እንቅስቃሴ እንዲኖር በማድረግ እና የከተማዋን ደህንነት በመጠበቅ ረገድም ከፍተኛ ሰራ መሰራቱንም ገልፀዋል፡፡
የግል ዘርፉን በማሳተፍ እና የውጭ ምንዛሪን በሚታደግ መልኩ የተከናወኑት እነዚህ የልማት ስራዎች ዝቅተኛውን ማህበረሰብ ሳይቀር ፍትሃዊ ተጠቃሚ ያደረጉ ናቸው ሲሉም አብራርተዋል፡፤።
እነዚህ በልዩ ትኩረት የተከናወኑ የልማት ስራዎች አዲስ አበባ የአፍሪካ መዲናነቷን እንድታስቀጥልና ለሌሎች የአፍሪካ ሀገራትም አርአያ እንድትሆን የሚያስችል መሆኑ ምክትል ከንቲባ አቶ ጃንጥራር አባይ ገልፀዋል፡፡
Comments
ምንም አልተገኘም.
አስተያየቶችዎን ይተዉት.