የአዲስ አበባ ለውጥ ያስደነቃቸው አፍሪካውያን
በመዲናዋ እየታየ ያለው ፈጣን የከተማ ልማት እና የውበት ለውጥ ለሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ትልቅ ተሞክሮ እንደሚሆን በ39ኛው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባዔ ላይ የታደሙ የተለያዩ ሀገራት ተወካዮች ገለጹ።
አዲስ አበባን ለመጀመሪያ ጊዜ ከስድስት ዓመታት በፊት ጎብኝተው እንደነበር ያስታወሱት
ከኢስዋቲኒ የመጡት የጉባዔው ተሳታፊ ኪንታፒ ሮቢንስ፤ አሁን ያገኟት ከተማ ግን ፈጽሞ የተለየች መሆኗን ተናግረዋል።
"አዲስ አበባ በየጊዜው እየተዋበች እና ንፁህ እየሆነች መጥታለች" ያሉት ተሳታፊው፤ ይህ ለውጥ በአጭር ጊዜ ውስጥ መመዝገቡ እጅግ አስደናቂ እንደሆነ አግራሞታቸውን ገልጸዋል።
አዲስ አበባ እያሳየችው ያለው ዕድገት ለሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ምሳሌ ሊሆን የሚችል ሲሆን፤ ለዚህም ጠንካራ የፖለቲካ ቁርጠኝነት አስፈላጊ መሆኑንም ጠቁመዋል።
ሌላዋ የጉባዔው ተሳታፊ ከደቡብ አፍሪካ የመጡት ሲተን በሌሞ በበኩላቸው፤ ከተማዋ የቱሪዝም መዳረሻዎቿን በማስፋት ለነዋሪዎችም ሆነ ለጎብኚዎች ምቹ እየሆነች መምጣቷን አድንቀዋል።
በመዲናዋ እየታየ ያለው ለውጥ የአፍሪካን ብልፅግና ከሚያልመው "አጀንዳ 2063" ጋር ቀጥተኛ ትስስር እንዳለው የገለጹት ሲተን በሌሞ፤ አፍሪካ ሕልሟን ለማሳካት የሁሉንም ዜጎች ብርቱ ጥረት ትፈልጋለች ብለዋል።
በተለይም በቱሪዝም እና በኢንቨስትመንት ዘርፎች ላይ ትኩረት ተደርጎ ሊሠራ እንደሚገባም አመልክተዋል። አፍሪካውያን በሚያሰባስቧቸው የጋራ እሴቶች ላይ አተኩረው ሊሠሩ እንደሚገባም አፅንኦት ሰጥተዋል።
Comments
ምንም አልተገኘም.
አስተያየቶችዎን ይተዉት.