የአቅርቦት ችግር እንዳይፈጠርና ገበያው በተረጋጋ ሁኔታ እንዲካሄድ ግብረ ሀይሉ በአከናወነው ስራ አመርቂ ውጤት መመዝገቡ ተገለጸ።
የማዕከልና የክፍለ ከተማ የገበያ ማረጋጋት፣ ህገወጥ ንግድ ቁጥጥር እና “ኢትዮጵያ ታምርት” ግብረ ሀይል የሶስት ወራት የስራ አፈጻጸምና በቀጣይ የስራ አቅጣጫዎች ላይ ውይይት አካሂዷል።
ውይይቱን የመሩት የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ እና የግብረ ሀይሉ ሰብሳቢ የተከበሩ አቶ ጃንጥራር አባይ እንደገለጹት፣ በዚህ የረመዳን እና የአብይ ጾም ወቅት ገበያውን በተረጋጋ ሁኔታ ለማስቀጠል የአፈጻጸም ግምገማ ማድረግ ወሳኝ ነው ብለዋል።
በውይይቱም የኑሮ ውድነትን ለመቀነስ፣ ህገወጥ ንግድን ለመቆጣጠር፣ የልማት ትሩፋትን ለማሳደግ፣ ተኪ እና ኤክስፖርት ምርት አምራቾችን በእጥፍ ለማሳደግ የተሰሩ ስራዎችና የተገኙ ውጤቶች ላይ ትኩረት ተደርጓል።
ባለፉት ሶስት ወራት የተከናወኑ ተግባራት ሪፖርት ቀርቦም በሰፊው ውይይት ተካሂዶበታል፤ የግብረ ሀይሉ አባላትም አመርቂ ውጤት መመዝገቡን አረጋግጠዋል።
በአሁኑ ወቅት በገበያ ላይ ምንም ዓይነት የምርት እጥረት እንደሌለ በተደረገው ክትትል መረጋገጡንም የግብረ ሀይሉ አባላት ገልጸዋል።
ገበያውን በዘላቂነት ለማረጋጋትና የአቅርቦት እጥረት እንዳይፈጠር ምርቶችን በማከማቸት እና ፈጣን መበላሸት ያላቸውን ምርቶች ረዥም ጊዜ እንዲቆዩ የማዘመን ስራዎች ሊጠናከሩ እንደሚገባ አቶ ጃንጥራር አሳስበዋል።
በመጨረሻም፣ በሚቀጥለው በዓል ወቅት በምርቶች ላይ ያልተገባ የዋጋ ጭማሪ እንዳይፈጠር ግብረ ሀይሉ በቅንጅት የሚያደርገውን ክትትልና ቁጥጥር እንዲያስቀጥል አሳስበዋል።
Comments
ምንም አልተገኘም.
አስተያየቶችዎን ይተዉት.