የአድዋ ድል ታሪክ ዛሬም መንፈሱ ጽናት ነው!

image description
- ውስጥ Current Affairs    0

የአድዋ ድል ታሪክ ዛሬም መንፈሱ ጽናት ነው!

130ኛውን የአድዋ ድል በዓል፣ የአድዋ ዘማቾች መነሻ በሆነውና የጀግኖቻችንን የተጋድሎ ታሪክ በሚመጥን መልኩ እዲዘከር በገነባነው የአድዋ ድል መታሰቢያ ከከተማችን ወጣቶች ጋር በፓናል ውይይት አክብረናል።

“ከአኩሪ ታሪክ ወደ ብሩህ አድማስ“ በሚል መሪ ቃል በመላው ከተማችን በተለያዩ ኩነቶች እየተከበረ የሚገኘውን የዘንድሮውን የአድዋ ድል በዓል፤ በደምና በአጥንት ዋጋ ተከፍሎ ለጥቁር ህዝቦችና  በጭቆና ውስጥ ለነበሩ የሰዉ ልጆች ሁሉ የድል ጮራ የሆነውን አኩሪ ታሪካችንን፣ ከወጣቶቻችን ጋር በታላቅ ድምቀት ዘክረነዋል።

ከአድዋ ድል የምንማረው የአንድነት እና  የፅናትን አይበገሬነትና አሸናፊነት ነው። በወቅቱ የአመለካከትና የአስተሳሰብ ልዩነቶች የነበሩ ቢሆንም፣ አገር ተነካ ሲባል እንደ አንድ ልብ መካሪና እንደ አፍ አንድ ተናጋሪ ሆነው በአንድነና በጀግንነት ወራሪውን ኃይል ድል ነስተውታል።

በእኛም ዘመን የራሳችንን ትውልድ ተሻጋሪ ታሪክ ለመስራት የአድዋን መንፈስ ታጥቀን በፅናትና ሁላችንም በአንድነት ተግዳሮቶችን ተቋቁመን፣ የታላቁን የህዳሴ ግድብ ግንባታ በማከናወን የ“አይቻልም” መንፈስን ሰብረን የዳግማዊ አድዋን ታሪክ ሰርተናል። እንዲሁም በአረንጓዴ አሻራ፣ በስንዴ ልማትና  በከተሞቻችን ትራንስፎርሜሽን  የልማት አብዮቶች የዳግማዊ አድዋ ድሎችን ፈፅመናል።

የዛሬው ውይይትም  ወጣቱ ትውልድ የቀደምት አርበኞችን አደራ፣ ታሪክና ጀግንነት በመውረስ የኢትዮጵያን የብልጽግና ጉዞ እውን ለማድረግ ያለውን ቁርጠኝነት፣ ጽናትና አንድነት በከፍተኛ የአገር ፍቅር ስሜት የገለጸበት መድረክ ነበር። ይህ ትውልድ ለተግዳሮቶች ሳይበገር “አይቻልም" የሚለውን አስተሳሰብ በመቻል የቀለበሰ፣ የራሱን አንፀባራቂ ታሪክ የሰራ ፣ የታሪኩ አውራሽና ለአዳዲስ ድሎች የተዘጋጀ አሸናፊ ትውልድ ነው።

በቀጣይም  ወጣቱ የአድዋ ድል አደራ የሆነውን አንድነት በማጠናከር ፣ የኢኮኖሚ ሉአላዊነትን በማረጋገጥ ፣ ሰላምን በማስጠበቅና የባህር በር ፍትሐዊ ጥያቄ ምላሽ እንዲገኝ በማድረግ ረገድ  ሚናውን ይበልጥ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጧል ።

ከአኩሪ ታሪክ፣ወደ ብሩህ አድማስ!

ፈጣሪ ኢትዮጵያን እና ሕዝቦቿን ይባርክ!

ከንቲባ አዳነች አቤቤ


Comments

ምንም አልተገኘም.

አስተያየቶችዎን ይተዉት.