ዓድዋ አጉራ ዘለል ፖለቲካን እና መከፋፈልን ይጸየፋል፦ ፕሬዝዳንት ታየ አጽቀሥላሴ
የዓድዋ አስተምህሮ ኢትዮጵያዊነትን የሚያገዝፍ፣ ጠባብነትንና መከፋፈልን የሚጸየፍ ታላቅ መካነ እውቀት መሆኑን የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ታየ አጽቀሥላሴ ገለጹ።
ፕሬዝዳንቱ ባስተላለፉት መልእክት፤ የዓድዋ ድል ለሀገራዊ ፖለቲካ እና ለዲሞክራሲ ልምምዳችን እንደ ዋና መቃኛ ሊያገለግል እንደሚገባ ጠቁመው፣ ድሉ የግጭትን ግለት ለሚሹ እና የጦርነት ትርክት ብቻ አፋቸው ለሚለዋወጥ ወገኖች ሁሉ ግብረገብነትን የሚያስተምር መሆኑን ገልጸዋል።
"ጀግንነት ሰላምን ማጽናት፣ ሕዝብን መጥቀም እና ሀገርን ማበልጸግ ነው" ያሉት ፕሬዝዳንት ታየ፣ የዘመኑ ጀግና የነውጥ ጩኸትን የሚያሰማ ሳይሆን የመቻቻል፣ የእውቀት እና የጥበብ ድምጽን የሚያጎላ መሆን እንዳለበት አሳስበዋል።
ኢትዮጵያዊነት በዓድዋ ሚዛን ሲለካ በላብ የጠነከረ እና በአርቆ አሳቢነት የሚለመልም ሕያው ማንነት መሆኑን የገለጹት ፕሬዝዳንቱ፣ ትውልዱ ከዕለታዊ የፖለቲካ ስሌት ይልቅ የሀገርን ብሔራዊ ጥቅሞች ማዕከል እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል።
Comments
ምንም አልተገኘም.
አስተያየቶችዎን ይተዉት.