የከተማችን ተጨማሪ ድምቀት በሆነው ከኡራኤል - ቦሌ መድኃኔዓለም እስከ ቦሌ ቪአይፒ (VIP) ተርሚናል የሚያገናኘውን የኮሪደር ልማት፣ ለአካባቢው ተጨማሪ ውበት የሚያጎናፅፉ እና ለሕዝብ ከፍተኛ ጥቅም ያላቸውን ዘርፈ-ብዙ ሥራዎች አካትተን አጠናቀናል።
ይህ መስመር ቀደም ሲል ደረጃቸውን ያልጠበቁ የአስፋልት መንገዶች፣ የእግረኛ መንገድ እጥረት፣ የሳይክል መንገድ አለመኖር እና ከፍተኛ የመኪና ማቆሚያ (ፓርኪንግ) ችግር የነበረበት ፣ደራጃዉን የጠበቀ የስዌሬጅ እና የድሬነጅ መስመር ያልነበረዉ፣ እንደ ሸረረት ድር የተወሳሰቡ መብራት እና የቴሌኮም ገመዶች እንዲሁም የደህንነት ካሜራዎች ያልነበረዉ እንደነበር ይታወሳል። በተጨማሪም ምንም ዓይነት የስፖርት ሜዳዎችም ሆኑ የሕፃናት መጫወቻዎች ያልነበሩበት፣ የህንፃዎች ውበት በቆሻሻና ዕድሳት በማጣት እንዲሁም አላስፈላጊ በሆኑ ተለጣፊ ግንባታዎች ተሸፍኖ የቆየ ነበር።
ዛሬ ግን ለኮሪደር ልማቱ ምስጋና ይግባውና አካባቢው ለአይን ማራኪና ዘመናዊ መልክ ይዟል።
ፕሮጀክቱ የሚከተሉትን ዋና ዋና ስራዎች አካትቷል፦
• 5.3 ኪ.ሜ የአስፋልት መንገድ፦ 60 ሜትር ስፋት ያለውና በሁለቱም በኩል 4 መስመሮችን የያዘ፤
• የትራንስፖርት ተርሚናል፦ ዘመናዊ የታክሲና የአውቶቡስ ተርሚናሎች፤
• የእግረኛና የሳይክል መንገድ፦ 10.538 ኪ.ሜ የእግረኛ መንገድ (ከ5 እስከ 10 ሜትር ስፋት ያለው) እና 4 ኪ.ሜ የብስክሌት መስመር፤
• የመኪና ማቆሚያ፦ በመንግሥትና በግለሰቦች ትብብር በአንድ ጊዜ እስከ 2,000 መኪናዎችን (900 ከቤት ውጭ እና 1,100 በህንፃዎች ውስጥ) ማቆም የሚችሉ ስፍራዎች፤
• ደረጃዉን የጠበቀ የስዌሬጅ እና የድሬነጅ መስመር ዝርጋታ፣
• ዘመናዊ መብራት እና የደህንነት ካሜራዎች
• የኤሌክትሪክ ቻርጅ ጣቢያ፦ 3,442.38 ካሬ ሜትር ላይ ያረፈ የተሽከርካሪዎች ቻርጅ ማድረጊያ፤
• የትራንስፖርት መቆሚያዎች፦ 15 የታክሲና አውቶቡስ ማቆሚያዎች፤
• የንግድና መዝናኛ ስፍራዎች፦ 8 ካፌዎች ከሕዝብ መጸዳጃ ጋር፣ ፕላዛዎች እና ለአነስተኛ ንግዶች የሥራ ዕድል የፈጠሩ ሱቆች፤
• አረንጓዴ ልማት፦ 5 ፋውንቴኖችን ያካተቱ ውብ አረንጓዴ ስፍራዎች፤
• የስፖርት ማዘውተሪያዎች፦ የእግር ኳስና የቅርጫት ኳስ ሜዳዎች እንዲሁም የሕፃናት መጫወቻ ስፍራዎች፤
• የህንፃዎች ዕድሳት፦ ውበታቸው ተመልሶ የታደሱ ከ200 በላይ ሕንፃዎች ፣ በከፍተኛ ጥራትና ፍጥነት ተሰርተዋል ።
እነዚህን ሁሉ አስደናቂ ተግባራት ሦስት ወራት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ አጠናቅቀን ለሕዝብ አገልግሎት ክፍት በማድረጋችን ታላቅ ደስታ ይሰማናል። ይህ ፕሮጀክት የከተማችን ብቻ ሳይሆን የሀገራችን ኩራትና ገጽታን የሚቀይር ስኬት ሆኗል። ለበርካታ ዜጎች የሥራ ዕድል ከመፍጠሩም በላይ የንግድ እንቅስቃሴውን በእጅጉ አነቃቅቷል፤ ወደፊትም የተሻለ ውጤት እንደምናገኝበት ሙሉ እምነት አለን።
ከእኛ ጋር በመሆን በትጋት የደከማችሁ አመራሮች፣ ሠራተኞችና ባለሙያዎች፣ በ24/7 የሥራ ባሕል ቀንና ሌሊት የለፋችሁ ሁሉ ምስጋና ይገባችኋል። እንዲሁም በመስመሩ ላይ ያላችሁ ባለሀብቶች፣ ነጋዴዎች፣ የቤትና የሕንፃ ባለቤቶች ሌት ተቀን ከጎናችን በመቆም ላደረጋችሁት ከፍ ያለ ትብብርና ማበረታቻ ምስጋናችን የላቀ ነው።
ፈጣሪ ኢትዮጵያን እና ሕዝቦቿን ይባርክ!
ከንቲባ አዳነች አቤቤ
Comments
ምንም አልተገኘም.
አስተያየቶችዎን ይተዉት.