ከመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት የተሰጠ የሀዘን መግለጫ
በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በጋሞ ዞን ጋጮ ባባ ወረዳ ላካ ቀበሌ መጋቢት 1 ቀን 2018 ዓ.ም በጣለው ከባድ ዝናብ ምክንያት በተከሰተ የመሬት መንሸራተት አደጋ በዜጎቻችን ላይ በደረሰው የህይወት መጥፋትና መፈናቀል የኢፌዴሪ መንግሥት ኮሙኒኬሽን የተሰማውን ጥልቅ ሀዘን ይገልጻል።
በዚህ አሰቃቂ አደጋ የ52 ወገኖቻችን ህይወት ማለፉ የተረጋገጠ ሲሆን፣ መንግሥት ለሟች ቤተሰቦች፣ ለወዳጅ ዘመዶቻቸው፣ ለጋሞ ዞን እና ለመላው የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ሕዝብ ልባዊ መጽናናትን ይመኛል።
በአሁኑ ወቅት የፌዴራልና የክልል ከፍተኛ አመራሮች በአደጋው ስፍራ በመገኘት የተጎዱ ወገኖችን የማጽናናትና የድጋፍ ስራዎችን በቅርበት እየተከታተሉ የሚገኙ ሲሆን በአደጋው ከመኖሪያ ቀያቸው ለተፈናቀሉ ወገኖች የሚያስፈልጉ መሠረታዊ ቁሳቁሶችና የምግብ አቅርቦት በአስቸኳይ እንዲደርስ ክልሉ ከፌዴራል አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ጋር በመቀናጀት ሰፊ የርብርብ ሥራ እየተከናወነ ይገኛል ።
መንግሥት ጊዜያዊ ድጋፍ በማድረግ ብቻ ሳይወሰን፣ ተጎጂዎችን ወደ ቀደመ ኑሯቸው ለመመለስና በዘላቂነት ለማቋቋም ልዩ ትኩረት ሰጥቶ የሚሰራ ሲሆን ተጨማሪ የህይወትና የንብረት ጉዳት እንዳይደርስ ለመከላከልም የስጋት ቀጠና ተብለው በተለዩ ስፍራዎች የሚገኙ የኅብረተሰብ ክፍሎችን የማንሳትና ወደ አስተማማኝ አካባቢዎች የማዘዋወር ሥራ በቅንጅትና በትኩረት እየተከናወነ ይገኛል።
በአሁኑ ወቅት ያለው ዝናባማ የአየር ሁኔታ መሰል አደጋዎችን ሊያስከትል ስለሚችል፣ በተለይም በደጋማና ለናዳ ተጋላጭ በሆኑ አካባቢዎች የሚኖሩ ዜጎች ከመንግሥት የሚሰጡ የጥንቃቄ መልዕክቶችንና መመሪያዎችን በአንክሮ በመተግበር አስፈላጊውን ጥንቃቄ እንዲያደርጉ መንግሥት ጥሪውን ያቀርባል ።
የኢፌዴሪ መንግሥት በአደጋው ሳቢያ የተጎዱ ወገኖችን መልሶ ለማቋቋም ከክልሉ መንግሥትና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት መስራቱን አጠናክሮ የሚቀጥል ሲሆን፤ ለሟች ወገኖቻችን ሰላማዊ እረፍትን፣ ለቤተሰቦቻቸውና ለወዳጅ ዘመዶቻቸውም መጽናናትን ይመኛል ።
የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት
Comments
ምንም አልተገኘም.
አስተያየቶችዎን ይተዉት.