የኑሮ ውድነትን ለመቀነስና ገበያውን ለማረጋጋት ከተማ አስተዳደሩ በትኩረት እየሰራ መሆኑ ተገለጸ።
በመዲናችን በሚገኙ በ11ዱም ክፍለ ከተሞች የረመዳን ፆም ፍቺ -ኢድ አልፈጥር በዓልን ምክንያት በማድረግ የበዓል ባዛር በይፋ ተከፈቷል፡፡
በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ መሳለሚያ አካባቢ በተዘጋጀው ባዛርና ኤግዚቢሽን የከፈቱት የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ እና የኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ጃንጥራር አባይ እንደገለጹት ባዛሩ በከተማው የተለያዩ አካባቢዎች ተዘጋጅቶ ሸማቹ ማህበረሰብ የፍጆታ እቃዎችን በበቂ መጠንና በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲያገኝ ያለመ እንደሆነ ገልጸዋል።
ባዛሩ በዋናነት በበዓል ወቅት በሚቀርቡ የፍጆታ ምርቶች ላይ የሚኖር የምርት እጥረት እንዳይፈጠርና ምርቶችን በስፋት ለማቅረብ እንደተዘጋጀ አቶ ጃንጥራር ገልጸዋል።
ከተማ አስተዳደሩ የኑሮ ውድነትን ለመቀነስና ገበያውን ለማረጋጋት በትኩረት እየሰራ መሆኑን የገለጹት ምክትል ከንቲባ አቶ ጃንጥራር ፤ ይህ ተግባር በበዓል ወቅት ብቻ የሚከናወን ሳይሆን በቀጣይነት የሚከናወን መደበኛ ስራ መሆን እንዳለበት ገልጸዋል።
በተጨማሪም የክፍለ ከተማው አመራሮች በገበያ ላይ ምርቶች በስፋት እንዲቀርቡ በመስራት ይህን እንቅስቃሴ እንደ ዘወትር ስራ በመውሰድ እንዲያስፈጽሙ አሳስበዋል::
Comments
ምንም አልተገኘም.
አስተያየቶችዎን ይተዉት.