መንግሥት ሁሉንም የሃይማኖት ተቋማት በእኩልነት...

image description
- ውስጥ Current Affairs    0

መንግሥት ሁሉንም የሃይማኖት ተቋማት በእኩልነት እንደ ዕሴቶቻቸውና አስተምህሯቸው በፍትሃዊነት ያገለግላል!

ከሌሎች  የሀይማኖት  ተቋማት ጋር እንዳደረግነው  ሁሉ ዛሬ ከኢትዮጵያ ወንጌላውያን፣ ከካቶሊክ እና ከሰባተኛ ቀን አድቬንቲስት ቤተክርስቲያናት መሪዎች ጋር “የሃይማኖት ተቋማት በመደመር መንግሥት እይታ” በሚል መሪ ሀሳብ ፍሬያማ ውይይት አካሂደናል።
ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት፣ የካቶሊክ እና የሰባተኛ ቀን አድቬንቲስት ቤተክርስቲያን በሰላም፣ በልማትና በትውልድ ግንባታ ሂደት ውስጥ የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት እንዲዳብር፣ አንድነት እንዲጠነክር፣ ትውልድ እንዲማር ፣ በስነምግባር  እንዲታነፅ ፣ ታሪክንና ቅርስን በመጠበቅ  እንዲሁም ለዓለም በማስተዋወቅ ረገድ ከፍተኛ ሚና አበርክተዋል። በተጨማሪም ቴክኖሎጂን ወደ ሀገር በማስገባትና የሥራ ባሕልን በማበረታታት ረገድ ከሌሎች የሀይማኖት ተቋማት ጋር በመሆን ወሳኝ አስተዋጽኦ አበርክተዋል።

በታሪክ ብቻ ሳይሆን ባለፉት የለውጥ ዓመታትም ተቋማቱ በከተማችን ሁለንተናዊ የሰላም ግንባታ፣ የልማት እና የብልጽግና ጉዞ ላይ እያበረከቱት ያለው ተሳትፎ ጉልህ ነው። በመድረኩ ለሕዝቦች ትስስር መጎልበት፣ በማኅበራዊ ልማትና በበጎ ፈቃድ ሥራዎች ተሳትፎ፣ የሥራ ባሕልን በማስረጽ፣ ትውልድን በሥነ ምግባር በመገንባት፣ የበጎነት  ስራ መስራት እንዲለመድ በማድረግ፣ ለመልካም አስተዳደርና አገልግሎት አሰጣጥ መጎልበት እንዲሁም ሰላምን በማስፈንና ሕገወጥነትን በመከላከል ረገድ ለኢትዮጵያ ብልጽግና እና ለብሔራዊ ጥቅም በጋራ ለመቆም ጠቃሚ ውይይት  አድርገናል።

በውይይታችን የተነሱ በስራ ሂደት ያጋጠሙ አንዳንድ ክፍተቶችን እና እንግልቶችን በቀጣይ በትብብር ለማረም የሚያስችል ምቹ መደላድል የፈጠረ ውጤታማ መድረክም ነበር። ይህ መድረክ በየክፍለ ከተማው ሲካሄዱ የቆዩ ውይይቶች ማጠቃለያ ሲሆን፣ የመንግሥትንና የሃይማኖት ተቋማትን ሚና እና ድርሻ በግልጽ ለይቶ ያስቀመጠ ነው።

ክቡራን የወንጌላውያን ፣ የካቶሊክ እና የኢትዮጵያ የሰባተኛ ቀን አድቬንቲስት ቤተክርስቲያን መሪዎች ላደረጋችሁት ከፍተኛ ተሳትፎና ለሰጣችሁት ገንቢ ሐሳብ በራሴና በከተማ አስተዳደሩ ስም ከልብ አመሰግናለሁ።
ፈጣሪ ኢትዮጵያን እና ሕዝቦቿን ይባርክ!
ከንቲባ አዳነች አቤቤ


Comments

ምንም አልተገኘም.

አስተያየቶችዎን ይተዉት.