የኢትዮጵያ አየር ኃይል ለመላው ኢትዮጵያዊያን የ...

image description
- ውስጥ Current Affairs    0

የኢትዮጵያ አየር ኃይል ለመላው ኢትዮጵያዊያን የኩራት ምንጭ የሆነ ታላቅ ተቋም ነው ሲሉ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለፁ።

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ የተመራው የአስተዳደሩ የስራ ኃላፊዎች በኢፌዴሪ አየር ኃይል ጉብኝት አድርገዋል።

በጉብኝቱም ላይ ከንቲባ አዳነች አቤቤ እንደተናገሩት አየር ኃይላችን በላቀ የስራ ትጋትና ጥራት እንደ ሀገር ያለንን ሀብት ተጠቅሞ ለውጥ ማምጣት እንደሚቻል አንዱ ማሳያ የሆነ ተቋም መሆኑን አውስተው በተለይም ከተጣለበት ሀገራዊ ተልዕኮ ባሻገር በግብርው ልማት በኩል ቀድሞ አላግባብ ጥቅም አልባ ተደርጎ የነበረውን የተቋሙን መሬት ወደ ልማት በመቀየር ያስመዘገበው ታላቅ ስኬት በሀገር ደረጃም አርዓያነት ያለው አኩሪ ስራ መሆኑንም ገልፀዋል።

በሰላም ወጥቶ ለመግባትም ብቻ ሳይሆን እንደ ሀገር ለተያያዝ ነው የልማት ጉዞ መከላከያችን ያፀናው ሰላም ወሳኝ መሆኑን ያስታወቁት ወ/ሮ አዳነች አቤቤ አያይዘውም የኢትዮጵያ አየር ኃይል ለመላው ኢትዮጵያዊያን የኩራት ምንጭ የሆነ ታላቅ ተቋም ነው ብለዋል። 

አቶ ጃንጥራር አባይ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ እና የእንዱስትሪ ቢሮ ኃላፊ በበኩላቸው የኢትዮጵያ አየር ኃይል ለሀገር ባለው ክብርና ዝና አንቱታን ያተረፈ ትልቅ ተቋም መሆኑን አውስተው የግዛት አንድነታችን እንዲሁም ሉዓላዊነታችን በማስጠበቅ ለሀገራችን መድህን የሆነ አንጋፋው የአቭዬሽን ተቋም መሆኑንም ጠቁመዋል።

ቢሾፍቱ በሚገኘው የአየር ኃይል መምሪያ ግቢ ውስጥ እየተከናወነ ያለው የግብርና ልማት አስተዳደሩ ለጀመረው የሌማት ትሩፋትም ጭምር በአርዓያነት የሚወስዱት መሆኑን የጠቆሙት አቶ ጃንጥራር አባይ ለዚ ሁሉ የተቋሙ ሰኬት አሻራቸውን ላኖሩ አመራሮችና አባላት ምስጋናቸውን አቅረበዋል።

የኢፌዴሪ አየር ኃይል ዋና አዛዥ ሌተናል ጄኔራል ይልማ መርዳሳ እንደገለጹት በሀገራችን የተጀመረው ተቋማትን ውብ እና ፅዱ አድርጎ የመገንባቱ ተግባር በአየር ኃይል ይበልጥ ተጠናክሮ መቀጠሉን ገልፀው የክብርት ከንቲባዋና ካቢኔያቸው በተቋሙ ያደረጉት ጉብኝት ትልቅ ፋይዳ ያለው የሞራል ስንቅ መሆኑንም ተናግረዋል።

ከተቋማዊ ሪፎርሙ ወዲህ የአዲስ አበባ አስተዳደር በርካታ እገዛዎችን ሲያደርግ መቆየቱን ያስታወቁት ሌተናል ጄኔራል ይልማ ለተደረገላቸው ድጋፍ ሁሉ የከተማ አስተዳደሩ በተለይም ለክብርት ከንቲባዋ ልዩ አድናቆት እና ክብር እንዳላቸውም ገልፀዋል።

በዕለቱ የግብርናውን ልማት እና ሌሎች ከለውጡ ወዲህ የተሰሩ መሰረተ ልማቶችን ክብርት ከንቲባዋና ካቢኔያቸው ተዘዋውረው ተመልከተዋል።


Comments

ምንም አልተገኘም.

አስተያየቶችዎን ይተዉት.