ውብ ስፍራዎች ለላቀ ተሰጥኦ፤ የመዲናዋ ወጣቶች...

image description
- ውስጥ Current Affairs    0

ውብ ስፍራዎች ለላቀ ተሰጥኦ፤ የመዲናዋ ወጣቶች የኪነ-ጥበብ ፌስቲቫል በአራዳ ፓርክ

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ከ11ዱም ክፍለ ከተማ የተውጣጡ ወጣቶች የተሳተፉበትና ልዩ ልዩ የኪነ-ጥበብ ስራዎች የቀረቡበት ደማቅ ፌስቲቫል በአራዳ ፓርክ አካሄደ።

ይህ በልዩ ሁኔታ የተዘጋጀው መድረክ ወጣቶች ያላቸውን የፈጠራ አቅም እንዲያሳዩ ከመቻሉም በላይ በከተማዋ የተገነቡ የኮሪደር ልማት ውጤቶች ለወጣቶች ሁለንተናዊ እድገት ያላቸውን ፋይዳ ያመላከተ ሆኖ አልፏል።

በፌስቲቫሉ ላይ የተሳተፉ ወጣቶች በሰጡት አስተያየት፤ በመዲናዋ በኮሪደር ልማት የተገነቡ ዘመናዊ የመዝናኛ ስፍራዎች ተሰጥኦቸውን በነፃነት እንዲያጎለብቱና የእርስ በእርስ ማህበራዊ ግንኙነታቸውን እንዲያጠናክሩ ትልቅ መሰረት መጣላቸውን ገልጸዋል። 

ወጣቶቹ በመድረኩ ላይ በስነ-ጽሁፍ፣ በስነ-ስዕል፣ በኪነ-ጥበብ እና በስፖርታዊ ፌስቲቫሎች ያላቸውን ከፍተኛ ብቃት ያቀረቡ ሲሆን፣ እነዚህ አዳዲስ የልማት ስራዎች ለኪነ-ጥበብ ስራዎቻቸው መነሳሳትን እንደፈጠሩላቸውና ለፈጠራ ስራ ምቹ ከባቢ መፍጠራቸውን በዝርዝር አስረድተዋል።

በአራዳ ፓርክ የተከናወነው ይህ የኪነ-ጥበብ ፌስቲቫል ወጣቶች  ከተለያዩ  ክፍለ ከተሞች በመምጣት ልምድ እንዲለዋወጡና በጋራ እንዲሰሩ ምቹ አጋጣሚ መፍጠሩ ተመላክቷል።

የአዲስ አበባ  ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ መሰል መድረኮች ወጣቶች በትርፍ ጊዜያቸው ገንቢ ተግባራት ላይ እንዲሰማሩ፣ ተሰጥኦአቸውን ለህዝብ እንዲያስተዋውቁና በከተማዋ በሚከናወኑ የልማት ስራዎች ላይ ባለቤትነት እንዲሰማቸው ለማድረግ ያለመ መሆኑን አስታውቋል።

 በቀጣይም  የኮሪደር ልማት መዝናኛ ስፍራዎች ለወጣቶች የክህሎት ማሳያና የተሰጥኦ ማበልጸጊያ ማዕከል በማድረግ ተከታታይ ዝግጅቶች እንደሚከናወኑ ተጠቁሟል።


Comments

ምንም አልተገኘም.

አስተያየቶችዎን ይተዉት.