ዛሬ በአዲስ አበባ የመጀመሪያውን የኢትዮ-ጣሊያን የኮንስትራክሽን፣ የመሰረተ ልማትና የከተማ መልሶ ማልማት ፎረም የእኛ ሚኒስትሮች እና የጣሊያ የውጭ ጉዳይ ምክትል ሚኒስትርና የዓለምቀፍ ትብብር ሀላፊ በተገኙበት አስጀምረናል።
አሁን ላይ በመዲናችን የንግድ እንቅስቃሴ እያደገ፣ የኢንቨስትመንት ፍሰቱም በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ ይገኛል። አዲስ አበባ በፍጥነት እየተለወጠች በመሆኗ፣ ይህ የኢትዮ-ጣሊያን የኮንስትራክሽን፣ የመሰረተ ልማትና የከተማ መልሶ ማልማት ፎረም መካሄዱ ወቅታዊ፣ ትክክለኛና እጅግ አስፈላጊ ነው።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለግል ዘርፉና ለኢንቨስትመንት መስፋፋት ትልቅ ድጋፍ ያደርጋል። የጣሊያን ወንድሞቻችንና እህቶቻችን በዚህች በተለወጠች ከተማ ውስጥ ኢንቨስት እንዲያደርጉ ጥሪዬን አቀርባለሁ።
አዲስ አበባ የተለወጠችው በገፅታ ብቻ ሳይሆን ቢዝነስ ለመስራት አመቺና ቀላል በመሆኗም ጭምር ነው። ኢንቨስት ለማድረግ ስትመጡ በፈጣንና ቀልጣፋ አሰራር ለማስተናገድ እንደ ‘መሶብ’ ያሉ የአንድ ማዕከል ዲጂታል የመንግስት አገልግሎቶች ዝግጁ ናቸው። አስተዳደራችን የግል ዘርፉን ለመደገፍ እጅግ ቁርጠኛ ሲሆን፣ ይህ ፎረም ለዚህ ግብ ትልቅ አስተዋፅኦ እንደሚኖረው እርግጠኞች ነን።
ክቡራን የፎረሙ ተሳታፊዎች፤ በአዲስ አበባ የሚኖራችሁ ቆይታ ፍሬያማ እንዲሆን እመኛለሁ።
ፈጣሪ ኢትዮጵያን እና ሕዝቦቿን ይባርክ!
ከንቲባ አዳነች አቤቤ
Comments
ምንም አልተገኘም.
አስተያየቶችዎን ይተዉት.