ባለፉት 8 ወራት ያለደረሰኝ ሽያጭ ሲፈፅሙ በቁጥ...

image description
- ውስጥ Current Affairs    0

ባለፉት 8 ወራት ያለደረሰኝ ሽያጭ ሲፈፅሙ በቁጥጥር ስር ከዋሉ ተጠርጣሪዎች መካከል 55ቱ ላይ ከ1 ዓመት እስከ 2 ዓመት ከ6 ወራት እስራትና የገንዘብ ቅጣት መቀጣታቸው ተገለፀ።

የአዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮ ፍትሃዊ የግብር አሰባሰብ ስርዓት በማስፈን ለከተማዋ ልማት የሚውል ገቢ በብቃት ለመሰብሰብ በከተማችን በተለያዩ አካባቢዎች ያለደረሰኝ ሽያጭ በሚያከናውኑ ነጋዴዎች ላይ  ተከታታይ የኦፕሬሽን ተግባራት ሲያከናውን መቆየቱ ታወቃል፡፡

ቢሮው ባለፉት 8 ወራት በተለያዩ የስራ ዘርፎች በተካሄዱ የኦፕሬሽን ተግባራት በልዩ ልዩ የንግድ ዘርፎች ውስጥ ተሰማርተው ያለደረሰኝ ሽያጭ ሲፈፅሙ የተገኙ 294 ተጠርጣሪዎች እጅ ከፍንጅ መያዛቸውን ነው  የገለፀው፡፡

የኦፕሬሽን ተግባራቱ በከተማችን በተለያዩ አካባቢዎች በጎማና በመኪና መለዋወጫ፣ በኤሌክትሮኒክስ ዕቃዎች፣ በኮንስትራክሽ ግብአቶች፣ በስጋ ቤት፣ በግንባታ ዕቃዎች፣ በሱፍ ልብስ እንዲሁም በወለል ምንጣፍ ንግድ ላይ በተሰማሩ ነጋዴዎች ላይ የተካሄዱ መሆናቸው ተጠቁሟል፡፡

በአሁኑ ወቅትም ከእነዚህ ተጠርጣሪዎች መካከል 55ቱ ጉዳያቸው ለፍርድ ቤት ቀርቦ ውሳኔ የተሰጠባቸው ሲሆን ከ2 ዓመት ከ6 ወራት እስከ 1 ዓመት ብይን ተሰጥቶባቸዋል ብሏል፡፡

በፍርድ ቤት ውሳኔ የተላለፈባቸው ግለሰቦች የመንግሰትን ጥቅም ለማሳጣት ከታክስ አስተዳደር አዋጅ በተፃረረ መልኩ ያለደረሰኝ ሽያጭ በመፈፀም ወንጀል የፈፀሙ መሆናቸውም ለማወቅ ተችሏል፡፡

የተቀሩት 239 ተጠርጣሪዎች ደግሞ በአሁኑ ወቅት ጉዳያቸው በፖሊስና በአቃቢ እጅ መሆኑ የተጠቆመ ሲሆን በህግ ቁጥጥር ስር ከዋሉ ተጠርጣሪዎች መካከል በኢንቨስቲጌሽን ኦዲት ዳግም ተጠያቂ እንዲሆኑ የተደረጉም መኖራቸው ተመላክቷል፡፡

ቢሮው በቀጣይም ያለደረሰኝ ግብይትና የግብር ስወራን ለመከላከል፣ የንግድ ሥርዓቱን ፍትሀዊነት ለማረጋገጥ እንዲሁም የህግ የበላይነትን ለማስከበር  የኦፕሬሽን ተግባሩን ከፖሊስ ጋር በመቀናጀት በሌሎችም የስራ ዘርፎች አጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን ጠቁሟል፡፡

በመጨረሻም የንግዱ ማህበረሰብ ግብይቶችን በደረሰኝ ብቻ እንዲፈፅም ህብረተሰቡም በ7075 ነፃ የስልክ መስመር በመጠቀም መሰል ወንጀሎችን እንዲያጋልጥ ጥሪ አቅርቧል፡፡

#ፍትሐዊ_የገቢ አሰባሰብ፣ ለአዲስ አበባ ብልፅግና !!


Comments

ምንም አልተገኘም.

አስተያየቶችዎን ይተዉት.