በሀገራዊ ለውጡ ስምንተኛ ዓመት ዋዜማ ላይ፣ በአዲስ አበባ አምስተኛውን የ"አዲስ መሶብ" የአንድ ማዕከል ዲጂታል አገልግሎት ማዕከል በይፋ ሥራ አስጀምረናል።
አዲስ አበባ አሁን የደረሰችበት ሁለንተናዊ ለውጥና ዕድገት፣ በለውጡ መንግሥት ቁርጠኝነት የተመዘገቡ የመጋቢት 24 ውጤቶች ናቸው። ከኢትዮጵያ መዲናነት ተሻግራ የአፍሪካ ኩራት የሆነችውን አዲስ አበባን በተግባርም እንደ ስሟ ውብ ለማድረግ፣ የለውጡ መንግሥት ገቢር ያደረጋቸው የልማት ሥራዎች ታሪካዊና ዘመን ተሻጋሪ ስኬትን አስመዝግበዋል።
ከለውጡ መንግሥት ስኬቶች መካከል አንዱ የ"አዲስ መሶብ" ዲጂታል የአንድ ማዕከል አገልግሎት ነው። የመንግሥት ሥርዓታት በተለዋወጡ ቁጥር ቃል እየተገባ ለመለወጥ ጥረት ቢደረግም፣ ሳይለወጥ ቆይቶ ተገልጋዩን ሲያማርር የኖረውን፣ ስር የሰደደና በተንዛዛ ቢሮክራሲ የተተበተበውን አሰራር ከመሠረቱ የሚቀይር ነው። ጊዜ፣ ወጪና ጉልበት የሚባክንበትን እንዲሁም ጥራትና ቅልጥፍና የራቀውን አገልግሎት አሰጣጥ በተግባር በመለወጥ አዲስ ምዕራፍ መክፈት ተችሏል።
"ማገልገል ክብር ነው" በሚል መርህ በንጹህ የአገልግሎት መስጫ ቦታዎች፣ በንጹህ አዕምሮ እና በንጹህ እጅ ማገልገልን ይዞ መጥቷል።
ይህ ዛሬ ያስጀመርነው የአዲስ መሶብ ማዕከል፣ መርካቶን ጨምሮ ሰፊ የንግዱ ማህበረሰብ የሚንቀሳቀስበት አካባቢ በመሆኑ፣ ቀልጣፋና ፈጣን አገልግሎት በመስጠት ረገድ ትልቅ እፎይታን የሚፈጥር ይሆናል።
እያሰፋን ያለነው የዲጂታል የመንግሥት አገልግሎት መስጫ ማዕከል፣ ከከተማችን ነዋሪዎች ባሻገር ለዲፕሎማቶች፣ ለቱሪስቶችና ለኮንፈረንስ ተሳታፊዎች ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ ፈጣን አገልግሎት እንዲያገኙ የሚያስችል ጭምር ነው።
ይህ የአንድ መስኮት ዲጂታል አገልግሎት በታለመለት ጊዜ ተጠናቆ ለአገልግሎት እንዲበቃ ለደገፋችሁ በሙሉ፣ በራሴ እና በተገልጋዩ ሕዝብ ስም ከልብ አመሰግናለሁ።
ፈጣሪ ኢትዮጵያን እና ሕዝቦቿን ይባርክ!
Comments
ምንም አልተገኘም.
አስተያየቶችዎን ይተዉት.