ለትንሳዔ በዓል የሸቀጦች አቅርቦት እጥረት እንዳ...

image description
- ውስጥ Current Affairs    0

ለትንሳዔ በዓል የሸቀጦች አቅርቦት እጥረት እንዳይከሰት ቅድመ ዝግጅት ተጠናቋል፡- የአዲስ አበባ ከተማ ንግድ ቢሮ

የአዲስ አበባ ከተማ ንግድ ቢሮ የትንሳዔ በዓልን ምክንያት በማድረግ በከተማዋ የሸቀጦች አቅርቦት እጥረት እንዳይከሰትና ገበያው እንዲረጋጋ አስፈላጊው ቅድመ ዝግጅት መጠናቀቁን አስታውቋል።

የቢሮው ኃላፊ ወይዘሮ ሀቢባ ሲራጅ ዛሬ በሰጡት መግለጫ፤ ከተማ አስተዳደሩ በዓሉን ተከትሎ ሊከሰት የሚችለውን የፍላጎት መጨመር ታሳቢ በማድረግ ካለፈው ወር ጀምሮ ከተለያዩ ክልሎችና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመቀናጀት ምርት የማሰባሰብ ሥራ ሲያከናውን መቆየቱን ገልጸዋል።

ወቅታዊው ዓለም አቀፍ የነዳጅ ችግር በምርት ስርጭት ላይ ተፅዕኖ እንዳያሳድር የተቀናጀ ዝግጅት መደረጉን ኃላፊዋ አመላክተዋል፡፡

በዚህም ለኅብረተሰቡ አማራጭ የገበያ ቦታዎችን ለማቅረብ በተሰራው ሥራ በመንግሥት በተዘጋጁ 6 ዋና ዋና የግብርና ምርት መሸጫ ማዕከላት፣ በ246 የሰንበት ገበያዎችና በ2 ሺህ 56 የኅብረት ሥራ ማህበራት ሱቆች በቂ ምርት እንዲገባ መደረጉን ተናግረዋል።

በተለይም መሰረታዊ ሸቀጦችንና እንደ ዘይት ያሉ የኢንዱስትሪ ምርቶችን ለተጠቃሚው ለማድረስ ሰፊ የገበያ ትስስር መፈጠሩ የተገለጸ ሲሆን፤ የሥጋ ምርትን በተመለከተም ኅብረተሰቡ በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲያገኝ በህብረት ሥራ ማህበራት በኩል አንድ ኪሎ ሥጋ በ650 ብር እንዲቀርብ መወሰኑ ተመላክቷል።

ከዚሁ ጋር ተያይዞ በበዓሉ ወቅት የዋጋ ንረትና የንግድ ማጭበርበር እንዳይኖር ቢሮው በሁሉም የገበያ ማዕከላት፣ ባዛሮችና መደበኛ ሱቆች ላይ ቁጥጥር የሚያደርግ ግብረ ኃይል አሰማርቷል።

በዚህም መሰረት ያለአግባብ የዋጋ ጭማሪ በሚያደርጉ፣ በምርት ላይ ባዕድ ነገር በሚቀላቅሉና በሚዛን በሚያጭበረብሩ ነጋዴዎች ላይ ጥብቅ ሕጋዊ እርምጃ እንደሚወሰድ አስታውቋል።

ኅብረተሰቡ የምርት እጥረት ሳያጋጥመው በዓሉን እንዲያከብር የሚያስችሉ እነዚህ የገበያ ማረጋጋት ሥራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም ቢሮው አስታውቋል።

ለተጨማሪ የመረጃ አማራጮች

https://linktr.ee/addisababacommunication


Comments

ምንም አልተገኘም.

አስተያየቶችዎን ይተዉት.