የሳይንስ ፈጠራ አውደ ርዕዩች ልጆቻችን ዘመኑን የሚቀድሙ ሥሉጥ ፤ ተወርዋሪ ከዋክብት ፤ የምጡቅና ረቂቅ አስተሳሰብ ባለቤት ለለውጥ እንጂ ለነውጥ የማይጣደፉ ይሆኑ ዘንድ ምቹ መደላድልን ይፈጥራሉ - ዶ/ር ዘላለም ሙላቱ
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር 11ኛው ከተማ አቀፍ የሳይንስ ፈጠራ አውደ ርዕይ "በሳይንስና ፈጠራ የተካነ ትውልድ ለተምሳሌታዊ ሀገር!" በሚል መሪ ሀሳብ የተለያዩ ባለድርሻ አካላት በተገኙበት በአራዳ ፓርክ በድምቀት መካሄድ ጀምራል።
በአውደ ርዕዩ ላይ የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት ያተላለፉት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ሀላፊ ዶ/ር ዘላለም ሙላቱ የሳይንስ ፈጠራ አውደ ርዕዩች እንዲካሄዱ መደረጋቸው ልጆቻችን ዘመኑን የሚቀድሙ ሥሉጥ ፤ ተወርዋሪ ከዋክብት ፤ የምጡቅና ረቂቅ አስተሳሰብ ባለቤት ለለውጥ እንጂ ለነውጥ የማይጣደፉ ይሆኑ ዘንድ ምቹ መደላድልን የሚፈጥር መሆኑን ገልጸዋል፡፡
አውደ ርዕዩ ተማሪዎች በክፍል ውስጥ በንድፈ ሀሳብ የተማሩትን ትምህርት በተግባር ቀይረው ስራዎቻቸውን ለተመልካች የሚያሳዩበት እድል የሚመቻችበት መርሀ ግብር እንደመሆኑ ከትምህርት ቤት ጀምሮ በወረዳና ክፍለከተማ ደረጃ ሲካሄድ ቆይቶ በከተማ ደረጃ የተዘጋጀ የማጠቃለያ መርሀግብር መሆኑን በመጥቀስ ለሁለት ቀናት በሚቆየው በዚህ ዐውደ ርዕይ 3700 የተማሪዎች ፣ የመምህራን፣ የልዩ ፍላጎት ተማሪዎችና መምህራን እንዲሁም የጎልማሶች ትምህርት ተማሪዎች የፈጠራ ሥራዎች ለምልከታ መቅረባቸዉን አመላክተዋል፡፡
ዐውደ ርዕይ የፈጠራ ሥራና ምርምርን ለማሳደግ የተወሰደዉን ቁርጠኝነት ፤ እያንዳንዱ ተማሪ ዕውቀትን ተጠቃሚ ብቻ ሳይሆን ተጠባቢ መሆኑን አመላካች ነው ያሉት ሀላፊው ባለፉት ዓመታት በጥቂት ተሳታፊዎች ይቀርቡ የነበሩ የፈጠራና ምርምር ውጤቶች የብዙዎች ባህልና ጉጉት መሆኑን ጠቅሰው ይህም እያንዳንዱ ተማሪ በቅጥነተ ሕሊና እንዲያስብና ለችግሮች መፍትሔ የመስጠት ክህሎት እንዲያዳብር ዕድል የፈጠረ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ዛሬ በከተማ ደረጃ ለእይታ የበቃው ዐውደ ርዕይ ነገ በሀገርና በአህጉር ደረጃ ሊጎበኝ የሚችል የፈጠራ ሥራዎች ማሳያ ፤ የልቀት ሥራዎች ማቅረቢያ እንዲሆን ዛሬ ዋጋ ከፍሎ መሥራት ይጠበራል ያሉት ዶክተር ዘላለም የከተማው ነዋሪዎች ዛሬን ጨምሮ ለሁለት ቀን በአራዳ ፓርክ በሚካሄደው የሳይንስ ፈጠራ አውደ ርዕይ ተገኝተው የፈጠራ ስራዎቹ ባለቤት የሆኑትን ተማሪዎችና መምህራንን እንዲያበረታቱ ጥሪ አቅርበዋል።
Comments
ምንም አልተገኘም.
አስተያየቶችዎን ይተዉት.