እንኳን ለ2016 ዓ.ም የትንሣኤ በዓል በሰላም...

image description
- ውስጥ Current Affairs    0

እንኳን ለ2016 ዓ.ም የትንሣኤ በዓል በሰላም አደረሳችሁ! ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ

ኢየሱስ ክርስቶስ መከራና ሞት፤ ግፍና ሙስናን፤ ሲዖልና መቃብርን አሸንፎ የተነሣበትን የትንሣኤ በዓል በየዓመቱ እናከብራለን። ከበዓሉ በፊት የሕማማትን ሰሞን እናሳልፋለን። ሰሞነ ሕማማቱ ፈተናን፣ ስቃይን፣ ክህደትን፣ አሳልፎ መስጠትን፣ የክፉዎችን ኅብረት፣ የምናስብበት ነው። ሐሰት ያሸነፈች፣ እውነት የተሸነፈች መስላ የታየችበት ነው። ብዙዎች መሥዋዕትነትን ፈርተው የሸሹበት ነው። አንዳንዶችን የሚያልፍ ጎርፍ ወሰዳቸው፤ አንዳንዶችን የሚሰክን ማዕበል ነጠቃቸው። ጥቂቶች ከሕማማቱ አልፈው ትንሣኤውን ለመመልከት ቻሉ።

የከተማው ጩኸት እና የሐሰቱ ወሬ እንኳን በሩቅ የነበሩትን፣ ቅርብ የነበሩትንም አሸንፏቸዋል። የሆሳዕና ዕለት ደግፈው የወጡት ከሦስት ቀን በኋላ ሊቃወሙ ሲወጡ ምንም አልመሰላቸውም። ድጋፋቸውም ተቃውሟቸውም ሁለቱም የጥቅም እንጂ የመርሕ አልነበረም። ሁለቱም ከእውነታው የተጣሉ ነበሩ። 

ሕማማት የውስጥና የውጭ ጠላቶች ተባብረውበታል። በሌላ ጊዜ ለሞት የሚፈላለጉ አካላት እውነትን ለመስቀል ሲሉ ግን ተባብረው ቆመዋል።

ሰዎቹ ያልተረዱት አንድ እውነታ ነበር። ከሕማማቱ ይልቅ ትንሣኤው ይበልጣል፤ ይረዝማልም። ሕማማቱ አምስት ቀን ሲሆን ትንሣኤው ግን አስር እጥፍ ይሆናል። የአምስት ቀን ፈተና የሃምሳ ቀን ዋጋ አለው። በርግጥ የሕማማቱን ሽብርና ዋይታ፣ መከራና እንግልት ለተመለከተ ትንሣኤ የሚመጣ አይመስለውም። ትንሣኤው ግን የታመነና የተረጋገጠ ነው። 

የበለጠ ማረጋገጥ የሚቻለውም ጸንቶ እንደ ዮሐንስ በመቆም ብቻ ነው።ኢትዮጵያ በፈተና ውስጥ እያለፈች ነው። በፈተና ውስጥ የቆመች ሀገር ግን አይደለችም። በፈተና ውስጥ እያለፈች ያለች እንጂ። ወቅቱ ለኢትዮጵያ የሕማማት ሰሞን ይሆን ይሆናል። አራት ነገሮች ግን እውነት ናቸው። የመጀመሪያው የኢትዮጵያ ሕማማት አጭር መሆኑ፤ ሁለተኛው አጭር ቢሆንም ከባድ መሆኑ፤ ሦስተኛው ኢትዮጵያ ሕማማቱን ለማለፍ የሚያስችል ኃይል ያላት መሆኑ፤ አራተኛው ከአጭሩ ሕማማት በኋላ ረዥሙ የኢትዮጵያ ትንሣኤ የሚመጣ መሆኑ ነው።

የተነሣነው ኢትዮጵያ እንደምትፈተን ዐውቀንም፤ አምነንም ነው። ለዘመናት የኖሩ ስብራቶችንና ብልሽቶችን ልናክም ስንነሣ መንገዱ አልጋ በአልጋ አይሆንም። ከችግሩ ማትረፍ የለመዱ አካላት ዝም አይሉም፤ ኢትዮጵያ በማሽን እንደሚረዳ ሕመምተኛ ሆና በሞትና በሕይወት መካከል እንድትኖር የሚፈልጉ ኃይሎች ዐርፈው አይቀመጡም። 

ግን ሕማማቱን እኛ ካልተቀበልንላት ለኢትዮጵያ ማን ይቀበልላታል? የመከራውን ቀንበር ካልተሸከምንላት የሀገር ልጅነቱ የቱ ጋ ነው? “ኢትዮጵያ ኢትዮጵያ” እያሉ በስሟ ሲምሉ የነበሩ ብዙዎች ነበሩ፤ ከልባቸው ለቃላቸው ታምነው ልጅ የሆኗት ግን ጥቂቶች ብቻ ናቸው። አንዳንዶች በስሟ የሚገዘቱት እንጀራዋን ለመብላት እንጂ መከራዋን ለመካፈል አይደለም፤ በተቃራኒው እንጀራዋን በልተው ተረከዛቸውን አነሡባት።

የሕማማቱ ወቅት አጭር ቢሆንም ከባድ መሆኑን እናውቃለን። የኮሶ መድኃኒት እንዲያሽር ከተፈለገ በአንድ ጊዜ በከባዱ መወሰድ አለበት። በትንሽ በትንሹ ከተወሰደ አያሽርም። የኢትዮጵያም ሕማማት እንደዚሁ ነው። 

በፊስካል ፖሊሲ፣ በግብርና፣ በማኑፋክቸሪንግ፣ በውጭ ጉዳይ ፖሊሲ፣ በኅብረ ብሔራዊ አንድነት፣ ነጻነትን በማስተዳደር፣ በክልል አደረጃጀት፣ በሲቪል ሰርቪስ፣ በጋራ ትርክት ግንባታ፣ ወዘተ. የተረከብናቸው ውዝፍ ዕዳዎች ብዙ ናቸው። ወገባችንን አሥረን፣ እጅጌያችንን ሰብስበን መራራውን የኮሶ መድኃኒት ውጠን፣ እነዚህን ችግሮች ካልፈታናቸው ቆመው አይጠብቁንም። በፈጣኑ ዓለም ውስጥ ቀስ ብለን ልንሄድ አንችልም። ተጠንቅቀን ግን ፈጥነን፤ አስበን ግን ዋጋ ከፍለን መጓዝ አለብን። ይሄ ነው ሕማማቱን የሚያሳጥረው።

ኢትዮጵያ ሕማማቱን ለማለፍ የሚያስችል ኃይል አላት። ከዚህ በፊትም ብዙ አልፋለች፣ አሳልፋለች። የማይተዋት አምላክ አላት። የሚወዳት፣ የሚያስብላት ብቻ ሳይሆን የሚሞትላትም አመራር አላት። ዓላማ አይቶ ዋጋ የሚከፍል ሕዝብ አላት። አንጡራ ሀብት አላት። ይሄ የፈጣሪ፣ የአመራሩ፣ የሕዝቡ እና የአንጡራ ሀብቷ አራት ማዕዘናዊ ዐቅም፣ ሕማማቱን ማሳጠርና ማስቻል ብቻ ሳይሆን ቀጥሎ የሚመጣውን ፋሲካ ረዥም እንዲሆን ያደርገዋል።

ብርቱውን ይዘናል - እንበረታለን፤ ኃይል በሚሰጠው እንታመናለን። ንጽሕናንና ለሀገር ያለንን በጎ ራእይ መሠረት አድገን ቆርጠን እንሠራለን። የጥብርያዶስ ሞቅታም ሆነ የፕራይቶሪዮን ግቢ ጩኸት ከመንገዳችን አያቆሙንም። የሆሳዕና ድጋፍም ሆነ የዕለተ ዓርብ ተቃውሞ መንገዳችንን አያስቀይሩንም። የኢትዮጵያን እውነት ብቻ ተከትለን እንገሠግሣለን። በዚህም ሕማማቱን አሳጥረን የኢትዮጵያን የትንሣኤ ጊዜ እናረዝመዋለን።

በድጋሜ መልካም የትንሣኤ በዓል!

ኢትዮጵያ በልጆቿ ጥረት ታፍራና ተከብራ ለዘላለም ትኑር!!

ፈጣሪ ኢትዮጵያና ሕዝቦቿን ይባርክ!

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ 

ሚያዚያ፣ 2016 ዓ.ም


Comments

ምንም አልተገኘም.

አስተያየቶችዎን ይተዉት.