“በጎነት በተግባር በትንሣኤ ዋዜማ!”
የቦሌ ክፍለ ከተማ አስተዳደር የትንሣኤን በዓል ምክንያት በማድረግ በአዲስ መልክ የታደሱ የአቅመ ደካማ ቤቶችን ለተጠቃሚዎች አስተላለፈ፡፡
አስተዳደሩ ከአጋር ባለሀብቶች ጋር በመተባበር 70 የአቅመ ደካማ ወገኖችን የመኖሪያ ቤቶች ሙሉ በሙሉና በከፊል አድሶ ያስተላለፈ ሲሆን፣ በቤት ርክክብ ሥነ ሥርዓቱ ላይ በክብር እንግድነት የተገኙት በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሥራና ክህሎት ቢሮ ኃላፊ አቶ ጥራቱ በየነ ባደረጉት ንግግር መንግሥት የዜጎችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥና በችግር ውስጥ የሚገኙ ነዋሪዎችን የተሻለ ኑሮ እንዲኖሩ ለማስቻል በገባው ቃል መሠረት ዘርፈ ብዙ ተግባራትን እያከናወነ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡ “ባለፉት ዓመታት በተከናወኑ ሰው ተኮር ሥራዎቻችን በተጨባጭ የሕዝብን ተጠቃሚነት የሚያሳድጉ ስኬቶች ተመዝግበዋል” ያሉት አቶ ጥራቱ፣ በትንሣኤ በዓል ዋዜማ በቦሌ ክፍለ ከተማ ለአቅመ ደካማ ነዋሪዎች የተደረገው የቤት ስጦታም የዚህ ስኬት አንዱ መገለጫ መሆኑን በመግለጽ በቤቶቹ እድሳት ሥራ ላይ ድጋፍ ላደረጉ በጎ አድራጊ ባለሀብቶች እንዲሁም ሥራውን ላስተባበሩ አካላት በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ስም ምስጋና አቅርበዋል፡፡
የቦሌ ክፍለ ከተማ አስተዳደር ዋና ሥራ አስፈጻሚ ወ/ሮ ዓለምጸሐይ ሺፈራው በበኩላቸው የክፍለ ከተማው አስተዳደር ልበ ቀና በሆኑ ባለሀብቶችና ተቋማት ትብብር በችግር ውስጥ የነበሩ የክፍለ ከተማው አቅመ ደካማ ነዋሪዎች የቤት ችግራቸው እንዲፈታ ከፍተኛ ሥራ ማከናወኑን ገልጸው፣ ቤቶቻቸው የታደሱላቸው ወገኖች መጪውን የትንሣኤ በዓል በደስታና በምቾት እንዲያሳልፉ ለማስቻል በየበኩላቸው አስተዋጽኦ ላበረከቱ አካላት ምስጋና አቅርበዋል፡፡ ተጠቃሚ ወገኖችም በዓሉ የደስታና የሰላም እንዲሆንላቸው ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ በክፍለ ከተማው አስተዳደር ስም ምኞታቸውን ገልጸዋል፡፡
ከቤት ርክክቡ ጎን ለጎን ለተጠቃሚ የክፍለ ከተማው ነዋሪዎች የበዓል መዋያ ስጦታ ተበርክቶላቸዋል፡፡
ሚያዚያ 26/2016
Comments
ምንም አልተገኘም.
አስተያየቶችዎን ይተዉት.