"የኑሮ ውድነቱን በማረጋጋት እና የተረጋጋ ገበያ በመፍጠር ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ለማድረግ በርካታ ስራ ተሰርቷል"
አቶ ጃንጥራር አባይ
የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ እና የኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ኃላፊ
የገበያ ማረጋጋት፣ ህገወጥ ንግድ ቁጥጥር እና ኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ግብረ ኃይል ከህዳር እስከ ሚያዚያ ወር ባሉት 6 ወራት በተሰሩ ስራዎች ላይ ውይይት አካሂዷል።
ውይይቱን የመሩት የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ እና የግብረኃይሉ ሰብስቢ አቶ ጃንጥራር አባይ ባለፉት 6 ወራት የሰንበት ገበያዎችን የማስፋት፣ተጨማሪ የገበያ ማዕከላትን የመገንባት እና የከተማ ግብርናን የማስፋት ስራ በሰፋት እንደተሰራ ገልጸዋል።
የኑሮ ውድነቱን በማረጋጋት የተረጋጋ ገበያ በመፍጠር ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ለማድረግ አትክልት እና ፍራፍሬ፣ የግብርና እና የኢንዱስትሪ ምርቶች፣የእንስሳት ተዋጽኦ እና የፍጆታ ምርቶች በሰንበት ገበያዎች ፣ በገበያ ማዕከላት እና በህብረት ስራ ማህበራት በስፋት ሲቀርቡ እንደቆዩ ገልጸዋል።
አቶ ጃንጥራር አክለውም ግብረኃይሉ ገበያን ለማረጋጋት እና የኑሮ ውድነትን ለመቀነስ የጀመረውን ስራ አጠናክሮ ማስቀጠል እንዳለበት ገልጸው በነበረው ቅንጅታዊ አሰራር ውጤታማ ስራ መስራት እንደተቻለ ጠቁመዋል።
ህብረት ስራ ማህበራት ምርቶችን በስፋት መያዛቸውን እና ማቅረባቸውን እንዲሁም ለህብረተሰቡ በትክክል ተደራሽ መሆናቸውን ግብረኃይሉ መከታተል እንዳለበት ገልጸዋል።
በህገወጥ ስራ ላይ በተሰማሩ አካላት ላይ ህግ የማስከበር ስራው ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ምክትል ከንቲባው አሳስበዋል።
Comments
ምንም አልተገኘም.
አስተያየቶችዎን ይተዉት.