የከተማዋን ነዋሪዎች የኑሮ ውድነት ጫና ለማቃለል የሚያስችል ዘመናዊ ሁለገብ የገበያ ማዕከል መዘጋጀቱን ከንቲባ አዳነች አቤቤ አስታወቁ
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ የከተማዋን ነዋሪዎች የኑሮ ውድነት ጫና በከፍተኛ ሁኔታ ለማቃለል የሚያስችል እና ዘመናዊ አገልግሎቶችን ያካተተ አዲስ ሁለገብ የገበያ ማዕከል መዘጋጀቱን አስታውቀዋል።
ከንቲባዋ እንደገለጹት፣ ይህ ማዕከል ለለሚ ኩራ፣ ለቦሌ እና ለየካ ክፍለ ከተሞች ነዋሪዎች አማካይ ስፍራ በሆነው ሰሚት ዋና መንገድ ላይ የሚገኝ ለግብይት እጅግ ምቹ የሆነ ስፍራ ነው።
ገበያ ማዕከሉ ማኅበረሰቡ ለዕለት ፍጆታ የሚጠቀምባቸውን የሰብል ምርቶች፣ አትክልትና ፍራፍሬዎች፣ የበርበሬና የቅመማ ቅመም እንዲሁም የኢንዱስትሪ ምርቶችን በአንድ ቦታ ማግኘት የሚያስችል ዘመናዊ የአንድ ማዕከል የግብይት ሥርዓትን እውን ያደረገ መሆኑን ከንቲባ አዳነች አብራርተዋል።
ከዚህም በተጨማሪ ማዕከሉ የኑሮ ውድነትን የሚያቃልሉ ዘመናዊ ማሞቂያ እና ማቀዝቀዣ ያላቸው 221 መጋዘኖችን፣ የችርቻሮ ሱቆችን፣ ሱፐር ማርኬቶችን፣ ወፍጮ ቤቶችን እና በአንድ ጊዜ 250 ተሽከርካሪዎችን ማስተናገድ የሚችል ሰፊ የፓርኪንግ አገልግሎትን ያካተተ መሆኑ ተገልጿል።
በዚህ ዘመናዊ የገበያ ማዕከል የሚቀርቡት የተለያዩ ምርቶች ከ15 እስከ 20 በመቶ በሚደርስ የዋጋ ቅናሽ ለሸማቹ የሚቀርቡ መሆናቸውን የገለጹት ከንቲባዋ፣ ይህም ዋጋ የሚያንረውን ሕገ-ወጥ የደላላ ሰንሰለት በመበጣጠስ ከአምራቹ ያልተቋረጠ ምርት በቀጥታ ለገበያ እንዲቀርብ በማድረግ የከተማዋን ነዋሪዎች የኑሮ ጫና በከፍተኛ ደረጃ የሚያቃልል መሆኑን በአጽንኦት አስገንዝበዋል።
Comments
ምንም አልተገኘም.
አስተያየቶችዎን ይተዉት.