ምርጫው ሰላማዊ፣ ዴሞክራሲያዊና ነጻ በሆነ መንገድ እየተካሄደ ነው - የአዲስ አበባ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ም/ቤት
7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ሰላማዊ፣ ዴሞክራሲያዊና ነጻ በሆነ መንገድ እየተከናወነ መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት አስታወቀ።
ምክር ቤቱ ይህንን የገለጸው በኢትዮጵያ የምርጫ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ በተቋቋመውና የምርጫ ሂደቱን በቀጥታ በሚከታተልበት የክትትል ክፍል በሰጠው መግለጫ ነው።
በመግለጫው፤ መራጩ ሕዝብ የዴሞክራሲ ሥርዓት እንዲሰፍን ከፍተኛ ጨዋነት በተሞላበት መልኩ ከሌሊቱ 9 ሰዓት ጀምሮ ከቤቱ በመውጣት ድምፅ ሲሰጥ መቆየቱን ጠቅሶ ለዚህም ምስጋና አቅርቧል።
የፖለቲካ ፓርቲዎች አማራጭ ሐሳባቸውንና ርዕዮተ-ዓለማቸውን በመገናኛ ብዙኃን አማካኝነት ካስተዋወቁ በኋላ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሕዝብ ለመራጭነት መመዝገቡን ያስታወሰው ምክር ቤቱ፣ ዛሬ እስከ እኩለ ቀን ባለው ሂደትም ሂደቱ ፍጹም ሰላማዊ ሆኖ መዋሉን ገልጿል።
ምክር ቤቱ በሁሉም ክፍለ ከተሞች ባለው መዋቅር አማካኝነት መረጃዎችን ሲለዋወጥና ሂደቱን ሲከታተል እንደነበር የጠቆመ ሲሆን፤ እስካሁን ባለው ሂደት የጸጥታ አካላት፣ ታዛቢዎች እንዲሁም በጎ ፈቃደኞች እያደረጉ ባለው ገለልተኛ አገልግሎት መደሰቱንም አስታውቋል።
በቀሪው የድምፅ አሰጣጥ ሂደትም ህዝቡ እስካሁን ባለው ጨዋነትና ትዕግሥት የዜግነት ግዴታውን እንዲወጣ የጋራ ምክር ቤቱ ጥሪውን አቅርቧል።
Comments
ምንም አልተገኘም.
አስተያየቶችዎን ይተዉት.