ዛሬ በምርጫ ማግስት የእንጦጦ ቀጨኔ የወንዝ ዳርቻ ልማት እና የአገልግሎት መስጫዎች በክቡር ጠቅላይ ሚኒስትራችን ተመርቀው ለህዝብ ክፍት አድርገናል።
የረዳን ፈጣሪ አምላክ የተመሰገነ ይሁን!!
በከተማችን ለሚገኙ ለብዙዎቹ ወንዞች መነሻና የከተማችን ሳምባ የሆነው ደን የሚገኝበት ከእንጦጦ እስከ ቀጨኔ ያለው አካባቢ ወደ ተፈጥሯዊ ይዘቱ ተመልሶ የአካባቢውን ማህበረሰብ አኩሪ የስራ ባህል የሚዘክሩ ሃውልቶችና ቅርሶች ተገንብተውለት አካባቢው ፍፁም ማራኪ እና የሚያስደንቅ ገፅታን ተላብስሶ ተጠናቋል።
የቀጨኔ አካባቢ ከዚህ ቀደም ለሰው ኑሮ ምቹ ያልሆነ፣ ለአደጋ የተጋለጠ እና የተጎሳቆለ አካባቢን መልሶ በማልማት ውስን የሆነውን የከተማዋን የመሬት ሀብት ለብዙሃን አገልግሎት እንዲሰጥ በሚያስችል መልኩ ለምቶ ለአገልግሎት ክፍት ሆኗል።
597 ሄክታር ቦታ እና 9.6 ኪሎ ሜትር የሚሸፍነው የእንጦጦ ቀጨኔ የወንዝ ዳርቻ ልማት ለመዝናኛ፣ ለንግድና ለተለያዩ ማህበራዊ ኩነቶች ተስማሚ በሆነ መልኩ የተገነባ ሰፊ የከተማ መናፈሻ ሆኗል።
በከተማ ግብርና ስራዎች 15 ሄክታር ቦታ በአረንጓዴ የተሸፈነ ሲሆን፣ ቀሪው ደግሞ በ210 ቀፎ ዘመናዊ ንብ እርባታ፣ በአበባ ጋርደን እና በእፀዋት ጋርደን ለምቷል።
እንጦጦ ቀጨኔ የወንዝ ዳርቻ ያካተታቸው ሌሎች መሰረተ ልማቶች፦
6.4 ኪሎ ሜትር የተሽከርካሪ መንገድ፣ 8 ኪሎ ሜትር የሳይክል መንገድ፣ 22 ክሎ ሜትር የእግረኛ መንገድ፣ 4 ኪሎ ሜትር ሃይኪንግ መንገድ፣ 39 ቼክ ዳም ተገንብተዋል።
2 አዲስ የተሽከርካሪ ድልድዮች ሲገነቡ፣ 3 ነባር የተሽከርካሪ ድልድዮች እድሳት ተደርጎላቸዋል። እንዲሁም ሌሎች የእረንጓዴ ልማት ጥንቅቅ ብለው ለምተዋል።
የከተማችን ነዋሪዎችን እንኳን ደስ አላችሁ እያልኩ፣ ይህንን ልዩ ሆኖ የተጠናቀቀ የእንጦጦ ቀጨኔ የወንዝ ዳርቻ ልማት አዕምሮችሁን ዘና አካላችሁን ፈታ እያደረጋችሁ እንድትገለገሉበት እና ረጅም አገልግሎት እንዲሰጥ እንድትንከባከቡት አደራ እላለሁ።
ፈጣሪ ኢትዮጵያና እና ህዝቦቿን ይባርክ
ከንቲባ አዳነች አቤቤ
Comments
ምንም አልተገኘም.
አስተያየቶችዎን ይተዉት.