7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ሕዝቡ ለዴሞክራሲ ሥርዓት...

image description
- ውስጥ Current Affairs    0

7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ሕዝቡ ለዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ያለውን ቁርጠኝነት በተግባር ያረጋገጠበት ነው!

የአዲስ አበባ ፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት

7ኛው ሃገራዊ ጠቅላላ ምርጫ መራጩ ሕዝብ ለዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ያለውን ቁርጠኝነትና ፍላጎት በተግባር ያረጋገጠበት መሆኑን የአዲስ አበባ ፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ገለጸ።

ምክር ቤቱ የ7ኛው ሃገራዊ ጠቅላላ ምርጫ ድምፅ አሰጣጥ ሂደት መጠናቀቁን አስመልክቶ ለመገናኛ ብዙሃን መግለጫ ሰጥቷል።

የአዲስ አበባ ፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢ አቶ ማሩ ጃኔ በሰጡት መግለጫ እንዳሉት፤ ምርጫው ግልጽነት እና ፍትሐዊነት ከመላበሱም ባሻገር በመራጩ የከተማዋ ሕዝብ ብቻ ሳይሆን በተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎችም ቅቡልነት ያሳየ ነው።

ምክር ቤቱ ከኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ የአዲስ አበባ ቅርንጫፍ ጋር በመቀናጀት ለምርጫው ስኬታማነት መሥራቱን አስታውሰው፤ ይህም ምርጫው ዴሞክራሲያዊና ሰላማዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን አብራርተዋል።

የምርጫ ሂደቱም እጅግ የተረጋጋ፣ የሰለጠነ እና የዴምክራሲ ሥርዓት ትግበራ ሂደትን ያጠናከረ ሆኖ ማለፉንም ጠቅሰዋል።

መገናኛ ብዙሃንም ለፓርቲዎች የሰጡት የአየር ሰዓት ፍትሐዊ፣ ግልጽና ለሁሉም ፓርቲዎች እኩል የመወዳደሪያ ሜዳ የሰጠ ነው ያሉት አቶ ማሩ፤ ይህም እያንዳንዱ የፖለቲካ ፓርቲ ያሉትን የፖሊሲ አማራጭ ሀሳቦች ያለምንም ገደብና ጫና ለሕዝቡ የሚያቀርብበት ዕድል መፍጠሩን አስረድተዋል።

የጸጥታ አካላትም ያለምንም ወገኝተኝነት ፍጹም ገለልተኛ በሆነና ሙያዊ አካሄዶችን በተከተለ መንገድ የአዲስ አበባ ምርጫ ጣቢያዎችንና የመራጩን ሕዝብ ደህንነት ሲጠብቁ መዋላቸውን ያስታወሱት ሰብሳቢው፤ የጸጥታ አካላት ያከናወኑት ተግባር ሊመሰገን የሚገባው ነው ብለዋል።

የድምጽ ቆጠራውና ውጤቱን የማደራጀት ሥራ የሚያከናወነው በሕጉ መሰረት የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ በመሆኑም ውጤቱ በከተማ ደረጃ በኦፊሴላዊ መልኩ እስኪገለጽ ድረስ በትዕግስት እንዲጠበቅ ምክር ቤቱ ጥሪውን ያቀርባል ነው ያሉት።

ማንኛውም ወገን የምርጫ ውጤቱን በጸጋ የመቀበል ታሪካዊና ሞራላዊ ግዴታ እንዳለበት አመልክተው፤ ቅሬታዎች ቢኖሩ እንኳን በሕጋዊ እና በሰላማዊ መንገድ ማቅረብ እንደሚገባ አሳስበዋል።

የአዲስ አበባ ፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ምክትል ሰብሳቢ አቶ ዘሪሁን ኮርሜ በበኩላቸው፤ በምርጫው አረጋዊያን፣ ሴቶች፣ ወጣቶችና ልዩ ልዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ያሳዩት ተሳትፎ እና ቁርጠኝነት ተምሳሌታዊ መሆኑን ተናግረዋል።

ለምርጫው ስኬት አስተዋጽኦ ላደረገው መራጩ ሕዝብ፣ ለምርጫ ቦርድ፣ የከተማዋ የጸጥታ አካላት ጨምሮ አስተዋጽኦ ላደረጉ አካላት በምክር ቤቱ ስም ምስጋና አቅርበዋል።

የምርጫ ውጤቱ ምንም ይሁን ምን የሕዝብ ድምጽ ልናከብር ይገባል ያሉት ምክትል ሰብሳቢው፤ የሰለጠነና ብስለት የተሞላበት የፖለቲካ አካሄድም ይሄው መንገድ ነው ብለዋል።

#ኢትዮጵያ_መርጣለች!


Comments

ምንም አልተገኘም.

አስተያየቶችዎን ይተዉት.