“የኢትዮጵያ ሕዝብ እና መንግሥት በራሳቸው ሊኮሩ ይገባል” - ኡሁሩ ኬንያታ
የአፍሪካ ኅብረት የምርጫ ታዛቢ ቡድን እና የኢጋድ ታዛቢ ቡድን 7ኛውን ጠቅላላ ምርጫ ሂደት አስመልክቶ የመጀመሪያ ዙር የግምገማ ውጤት ላይ መግለጫ ሰጥተዋል።
የአፍሪካ ኅብረት የምርጫ ታዛቢ ቡድን መሪ የሆኑት የቀድሞው የኬንያ ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ እና መንግሥት በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ላይ ባሳዩት ድንቅ የሆነ አፈጻጸም በራሳቸው ሊኮሩ ይገባል ብለዋል።
“ኢትዮጵያውያን ከማለዳው ጀምሮ በቁርጠኝነት ለመምረጥ ተሰልፈዋል፤ ይህን ታላቅ ሁነት በኢትዮጵያ የተለያዩ ቦታዎች ተመልክተነዋል፤ እስከ እኩለ ሌሊት ድረስ የታዘብነው ምርጫ በስኬት በመጠናቀቁ እንኳን ደስ አላችሁ ለማለት እወዳለሁ” ሲሉ አጠቃላይ ሁኔታውን ገልጸውታል።
“ኢትዮጵያውያን ታሪክ ይሠራሉ፤ ቀኝ ገዢዎችን በጋራ ተዋግተዋል፤ ይህም በአፍሪካ ብቸኛ ሀገር እንድትሆን አስችሏታል፤ የአፍሪካ የነፃነት ምልክቷ ኢትዮጵያ ነች” ብለዋል።
የአፍሪካ ኅብረት ምርጫውን ለመታዘብ ቀጠሮ ከያዘ ጊዜ ጀምሮ የምርጫውን ታማኝነት እና ዴሞክራሲያዊነት ስንከታተል ነበር ያሉት ኡሁሩ ኬንያታ፣ ምርጫ ቦርድ ቀደም ብሎ የሠራው ሥራ መራጮች ሳይደናገሩ ድምፅ እንዲሰጡ እንዳስቻለ አንሥተዋል።
በምርጫው ዕለት የፖለቲካ ፓርቲ ታዛቢዎች የምርጫውን ሂደት በነጻነት ሲከታተሉ እንደነበር ጠቁመው፣ “በዚህም የኢትዮጵያ ሕዝብ ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ያለውን ታላቅ ቁርጠኝነት የታዘብንበት ነበር” ብለዋል።
Comments
ምንም አልተገኘም.
አስተያየቶችዎን ይተዉት.